
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሰላም እና የጸጥታ ችግር የተሳሳተ የፖለቲካ አመለካከት ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ የስንፍና ፖለቲካ መንሰራፋቱን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የስንፍና ፖለቲካ ግጭት፣ ጸብ እና ተቃርኖን ይወልዳል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ያሉ ሰነፍ ፖለቲከኞች ሳይሠሩ መብላት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። ሥራ እንደማይወዱ እና ሥራ እንደማይሠሩም ተናግረዋል። አገልግሎት የማይሰጡ፣ ሥራ የማይሠሩ እና ግብር የማይከፍሉ ፖለቲከኞች መኖራቸውን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ያሉ አውርቶ አደር ፖለቲከኞች ካላጋጩ መብላት እንደማይችሉም አመላክተዋል። ግጭት ካልተፈጠረ በስተቀር ትርፍ እንደማያገኙም አንስተዋል።
ፍላጎቴን በኃይል አስፈጽማለሁ የሚል የፖለቲካ አካሄድ ሌላኛው ችግር መኾኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት። የተመረጠን መንግሥት በኃይል ማሸነፍ የሚፈልጉ፣ ኃይል በብቸኝነት የመጠቀም ሥልጣን የመንግሥት ብቻ መኾኑን የማይቀበሉ፣ በመግደል መሸነፍ እንጂ ማሸነፍ እንደሌለ የማያምኑ ፖለቲከኞች መኖራቸውን ገልጸዋል። የሃይማኖት አባቶችን እና ተማሪዎችን የሚገድሉ እንዳሉም አንስተዋል። በመግደል የሚሳካ ነገር እንደሌለም ገልጸዋል። የግድያ አካሄድ መቆም እንዳለበትም ተናግረዋል። ድህነትን ካልቀነስን እና ሥራ ካልፈጠርን የችግር አባባሽ ኾኖ ይቀጥላል ነው ያሉት።
ኋላቀርነትን እና ሥር የሰደደ ዘረኝነትን ማስተካከል እንደሚገባም ገልጸዋል። ከዘረኝነት ላይ የውጭ ጣልቃ ገብነት እና ባንዳነት ሲታከልበት ለጸጥታ ችግር መነሻ ይኾናል ነው ያሉት። ኢትዮጵያ ስትጋጭ ትርፍ እናገኛለን ብለው የሚያስቡ ኃይሎች መኖራቸውንም ተናግረዋል።በኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲከኞች ስለኾኑ ብቻ የታሠሩ ፖለቲከኞች እንደሌሉም ተናግረዋል። ሥልጣን ካልሰጣችሁን ዲሞክራሲ የለም የሚል አካሄድ እንደማይሠራም ገልጸዋል። በእኔ ስም ሰው አትግደሉ፣ ልጆቼ እንዳይማሩ አትከልክሉ ማለት አለበት ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ሕዝብ በዓደባባይ ወጥቶ በቃኝ ብሏል ብለዋል። የአማራ ሕዝብ መልዕክት አስተላልፏል፣ ለሕዝብ ጥያቄ የከበረ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል ነው ያሉት።ሰላም ሁልጊዜም አንጻራዊ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰላም ማለት የጥይት ተኩስ አለመኖር ብቻ አይደለም ነው ያሉት። በኢትዮጵያ አንጻራዊ ሰላም አለ፣ ነገር ግን ኢትዮጵያ የሚገባት ፍጹም ሰላም ነው፤ አሁንም ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዳይገቡ የሚያደርጉ ኃይሎች አሉ ብለዋል። የዜጎችን ሰላም የሚነሱ አካላትን በተባበረ ክንድ አደብ ማስገዛት ይገባል ነው ያሉት።
የፕሪቶሪያ ስምምነት ለትግራይ ሕዝብ እፎይታ አምጥቷል፣ ለኢትዮጵያ አዲስ ባሕል አምጥቷል፣ ለካ መንግሥት ማሸነፍ እና ማጥፋት እየቻለ ግን ሰላም ይበልጣል ብሎ ውጊያ አቁሞ ሥልጣን ይሰጣል የሚል ትምህርት ሰጥቷል ብለዋል።
የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ያለውን ጉዳይ በሰላም ለመፍታት ጽኑ አቋም እንዳለውም ተናግረዋል። የትግራይ ሕዝብ ጦርነት እንደማይፈልግም ገልጸዋል። መንግሥት ተወጥሯል በሚል ስሌት ግጭት ለመፍጠር የሚጥሩ ኃይሎች አሉ፣ ይህ ስህተት ነው፣ የኢትዮጵያን ታሪክ ዘወር ብሎ ያለማየት ችግር ነው ብለዋል። ግጭት ዳግም እንዳይጀመር መምከር እንደሚገባም ተናግረዋል። ውይይትን ማስቀደም እንደሚገባም አመላክተዋል።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን