ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥታዊ ሙስና ባለመኖሩ ልማት መምጣቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ተናገሩ።

14

ሕር ዳር፡ ሰኔ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ በበጀት ዓመቱ ትልቅ የሥራ አፈጻጸም ከታየባቸው ሴክተሮች ውስጥ የሥራ ዕድል ፈጠራ አንዱ መኾኑን ተናግረዋል። በዚህም 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች ሥራ ይዘዋል ብለዋል፡፡

ከእነዚህ ውስጥ በግብርናው የሥራ ዘርፍ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል አግኝተዋል ነው ያሉት፡፡ በአገልግሎት ዘርፍ ለ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሰዎች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢንዱስትሪው ዘርፍም 680 ሺህ ገደማ ዜጎች የሥራ ዕድል አግኝተዋል ነው ያሉት፡፡

በበጀት ዓመቱ ሥራ የያዘው 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሰው ቁጥር ትልቅ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ዘመናዊ በኾነ መንገድ ተቋሙ የጀመረው ሥራ ይበል የሚያሰኝ ነው ብለዋል። ነገር ግን ካለው የሥራ አጥ ቁጥር ክፍተት አንጻር ሰፊ ሥራ መሠራት እንዳለበት አመላክተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥታዊ ሙስና የለም ለዚህም ነው እየለማን ያለነው ነው ብለዋል፡፡ ነገር ግን ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ ሙስና ችግር ነው ብለዋል፡፡

ይህንን ለመቅረፍ በተደጋጋሚ በውይይት እና በሥልጠና ለመግባባት ሙከራ ስለመደረጉም አስገንዝበዋል፡፡ በዚህም ግን ችግሩን መቅረፍ አልተቻለም ነው ያሉት፡፡ ለዚህም ዋናው መፍትሄ ኾኖ የተገኘው የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ማድረግ ነው ብለዋል፡፡

ይህ ሪፎርም መሶብ በሚል በ8 ተቋማት 41 አገልግሎቶች የቨርችዋል አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት ተዘርግቷል ነው ያሉት፡፡ ቨርችዋል አገልግሎት አሰጣጡን በሁሉም ክልሎች በመገንባት እና በማጠናከር አገልግሎት አሰጣጡን በሪሞት ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡ ይህ ሲኾን እና የእጅ በእጅ መቀባበሉ ሲቆም ሙስናን መቀነስ ይቻላል ነው ያሉ፡፡

ከዚህ ውጭ በሕግ እና በመመሪያ ብቻ ሙስናን መከላከል በቂ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህም የመሶብ የተገልጋይ እርካታ ሲታይ 90 በመቶ ነው ይህንን አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በሰናይት በየነ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“ሰው ግብር የሚከፍለው ለራሱ እና ለሀገሩ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next article“የስንፍና ፖለቲካ ግጭት፣ ጸብ እና ተቃርኖን ይወልዳል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)