
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 26/2017 ዓ.ም
(አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የገቢ አሠባሠብን በተመለከተ ለተነሳላቸው ጥያቄ ማብራሪያ ሲሰጡ በዚህ ዓመት 900 ቢሊዮን ብር ገቢ መሠብሠቡን አንስተዋል። አጠቃላይ የሀገሪቱ ወጭ ግን 1 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ብር ነበር ብለዋል። በገቢ እና በወጭ መካከል 300 ቢሊዮን ብር ልዩነት ስለመኖሩም ጠቁመዋል።
ገቢ ከግብር ብቻ ሳይኾን ከተለያዩ አርዕስቶች እንደሚሠበሠብ ገልጸው በተለይም ከግብር የተሠበሠበው ገቢ ከሀገሪቱ ወጭ አንጻር ዝቅተኛ ነው ብለዋል። ሀገሪቱ ያላት አጠቃላይ ሃብት እና ከዚህ ሃብት የሚሠበሰበው ግብር ያልተመጣጠነ ስለመኾኑም አስረድተዋል።
ባለን ሃብት ልክ የግብር ገቢ መሠብሠብ እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ 46 ሺህ የሚኾኑ የታክስ ተመዝጋቢዎች የሚጠበቅባቸውን ግብር እንደማይከፍሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ አንስተዋል።
ከነጋዴዎች ውስጥ የኪሳራ ሪፖርት ያቀርባሉ፤ ገቢ እና ወጭያቸው ተመሳሳይ የኾነ እና ምንም አይነት ትርፍ እንደሌላቸው ይገልጻሉ፣ የተወሰኑት ደግሞ ሪፖርትም አያቀርቡም፣ በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ ንግድ ፈቃድ ወስደው ግብር መክፈል ከሚገባቸው ነጋዴዎች ውስጥ 37 በመቶ የሚኾኑት ብቻ ናቸው የሚከፍሉት ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ይህም 60 በመቶ የሀገሪቱን ገቢ መኾኑን ጠቁመዋል። ቀሪው 40 በመቶ ገቢ ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች የሚሠበሠብ ነው ብለዋል።የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የተጠናከረ የሥራ ለውጥ ውስጥ በመግባታቸው በዚህ ዓመት 2 ትሪሊየን ብር ገቢ አግኝተዋል። ከዚህ ውስጥ በመቶ ቢሊዮኖች ግብር ከፍለዋል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
የቀጣይ ዓመቱን የገቢ መጠን ለመጨመር ንግድ ፈቃድ ወስደው ግብር መክፈል ከሚገባቸው ነጋዴዎች ውስጥ ቢያንስ 50 በመቶው እንዲከፍሉ ማስቻል አለብን ብለዋል። ሰዎች ትልልቅ ልማቶችን እየሠሩ፣ ቅንጡ መኪናዎችን እየነዱ፣ ትልልቅ ግንባታዎችን እየሠሩ፣ ግብር መክፈል ላይ ግን ወደ ኋላ የማለት ባሕሪ እንደሚታይባቸው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ድርጊት ለሀገር ሲባል መታረም እንዳለበትም አሳስበዋል።
ለሀገራቸው ሲሉ ግብር የሚከፍሉ፣ ልማት የሚያግዙ ታማኝ ሰዎች ስለመኖራቸውም ጠቅሰዋል። ግብርን በተመለከታ አንደኛው ችግር የታክስ አሥተዳደር ሥርዓቱ መኾኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል። ይህን ሥርዓት ለማሻሻል እየተሠራ ነው ብለዋል።
የግብር ስወራ እና ለቁጥጥር የማይመች ገቢ እና ወጭ አያያዝም ሌሎች የገቢ አሠባሠብ እንቅፋቶች ናቸው ብለዋል። ይህ ችግር እንዲፈታ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ጠቅሰው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም አሥፈላጊውን እገዛ እንዲያደርጉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠይቀዋል።”ሰው ግብር የሚከፍለው ለራሱ እና ለሀገሩ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግድ ሥራ ላይ ያሉ ወገኖች በሙሉ በታማኝነት ግብር የመክፈል ልምምድን እንዲያሳድጉ መክረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን