
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በጤና እና በትምህርት ዘርፎች ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ጤናን በሚመለከት በኢትዮጵያ የሚገኙ የጤና ተቋማት ቁጥር 22ሺህ መድረሱን እና ከዚህ ውስጥ 6 ሺህ የሚኾኑት ከለውጡ በኋላ የተገነቡ እንደኾኑ ገልጸዋል፡፡
በጤናው ዘርፍ የግል ተቋማት ጥሩ አገልግሎት የሚሰጡ መኖራቸውን ተዘዋውረው ባደረጉት ምልከታ ማየታቸውን አንስተው ተስፋ ሰጭ ጉዳዮች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡ በተመሳሳይ ችግሮች መኖራቸውንም ገልጸዋል፡፡
የጤና ሙያተኞች ጥያቄ አላቸው አቅም በፈቀደ መጠን ምላሽ መስጠት እና ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የጤና አገልግሎት ለማሻሻል ጠንክሮ መሥራት አስፈላጊ ነውም ብለዋል፡፡ ትምህርትን በሚመለከት የተሻለ ትውልድ ለመቅረጽ ቅድመ መደበኛ ላይ በትኩረት መሥራት አስፈላጊ እንደኾነም አስረድተዋል፡፡
በዚህ ዓመት 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሕጻናት እና 29 ሺህ የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች በቅድመ መደበኛ የመቀበል አቅም ከፍ ማለቱን አንስተዋል፡፡ የመምህራንን ሥልጠና በተመለከተ እንደከዚህ ቀደሙ በጅምላ ሳይኾን በሚያስተምሩት የትምህርት አይነት እና የማስተማር ዘየ ትኩረት ያደረገ ሥልጠና በተያዘው ዓመት መጀመሩን ነው የገለጹት፡፡
ባለፈው ክረምት 68 ሺህ መምህራን ሠልጥነዋል በዚህ ክረምትም 80ሺህ መምህራን ይሠለጥናሉ ነው ያሉት፡። ይህም የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል አጋዥ መኾኑን አብራርተዋል፡፡ በጦርነት የተጎዱ ቦታዎች የትምህርት ተቋማትን ለመጠገን ሙከራ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
ከዚህም ባለፈ በትምህርት ሚኒስቴር 30 የሚደርሱ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ እንደኾነም ገልጸዋል፡፡ከኅብረተሰቡ ትምህርት ለትውልድ ተብሎ በተሠበሠበ ገንዘብም በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል።
የተማሪዎች መማሪያ መጽሐፍ ካሪኩለም ከመቀየሩ ጋር ተያይዞ መጽሐፍ ያልነበረ መኾኑን ጠቅሰው እስካሁን 46 ሚሊዮን መጽሐፍት ታትመው በሁሉም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አንድ መጽሐፍ ለአንድ ተማሪ ተዳርሳል ብለዋል፡፡ ይህም በትምህርት ዘርፍ ትልቅ እምርታ እንደኾነ ነው የገለጹት፡፡
በፍሬህይዎት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን