“እስከ ነሐሴ 2017 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ ከ20 ሺህ በላይ ፕሮጄክቶች ይመረቃሉ” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

21

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ እየሠጡ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ዜጎችን የቤት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ባለፉት አምስት ዓመታት 1 ሚሊዮን ገደማ ቤቶች መገንባታቸውንም አስታውቀዋል። አሁን 265 ሺህ ቤቶች እየተገነቡ መኾናቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ሁሉም እያላት መራብ እንደሌለባትም ተናግረዋል። ካልሠራን በስተቀር ኢትዮጵያን መለወጥ አንችልም ነው ያሉት። በእኛ ጊዜ ኢትዮጵያ ልመና ታቆማለች፣ የጀመረቻቸውን ፕሮጄክቶች ትጨርሳለች፣ የብልጽግናዋ መሠረት ይጣላል ብለዋል። እድገትና ብልጽግና መቆሚያ የሌለው ሂደት መኾኑን ተናግረዋል።

የኮሪደር ልማት ሥራዎች በቀላል የሚታዩ አለመኾናቸውን ገልጸዋል። የኮሪደር ልማት ሥራዎችን መደገፍ እንደሚገባም ተናግረዋል። የኮሪደር ልማት የከተሞችን ውበት እየቀየረ መኾኑንም አመላክተዋል። እስከ ነሐሴ 2017 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ ከ20 ሺህ በላይ ፕሮጄክቶች ይመረቃሉ ነው ያሉት። ፕሮጄክቶች ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ እንደኾኑም ተናግረዋል።

መከራ በበዛ ጊዜ ጠንካራ ትውልድ እንደሚፈጠር የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠንካራ ትውልድ ምቹ ሀገር ይሠራል ነው ያሉት። የሕዝብን ጥያቄ እየመለሱ መሄድ እንደሚገባም ተናግረዋል።

በታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“ሪፎርሙ የፋይናንስ ሴክተሩን አነቃቅቷል”
Next articleበጤና እና በትምህርት ዘርፍ ውጤታማ ሥራ መሠራቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ተናገሩ።