“1 ነጥብ 5 ቢሊየን ኩንታል ምርት መሠብሠብ ተችሏል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

7

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ እየሠጡም ይገኛሉ።

በበጀት ዓመቱ ግብርናው 6 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት እንዲያመጣ መታቀዱንም ገልጸዋል። በግብርና እንዲህ ዓይነት ዕድገት ማምጣት ለአጠቃላይ ዕድገት ከፍተኛ አሰተዋጽኦ እንደሚያደርግም ገልጸዋል። ለግብርና ልዩ ትኩረት የተሠጠበት ምክንያት ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ስላለባት ነው ብለዋል። አምርታ መብላት የማትችል ሀገር ሉዓላዊነቷን ለመጠበቅ ትቸገራለች ነው ያሉት።

ባለፉት ዓመታት 27 ሚሊዮን ዜጎች በሴፍቲኔት ታቅፈው እንደነበር የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በርካታ ዜጎች ራሳቸው አምርተው ከሴፍቲኔት ነጻ እየኾኑ ነው ብለዋል። 23 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ከሴፍቲኔት ነጻ ወጥተዋል፣ ይህ ትልቁ የማንሰራራት ማሳያ መኾኑን ገልጸዋል። በአጭር ጊዜ ውስጥ በሴፍቲኔት ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን ነጻ በማውጣት ዕድገትን ማረጋገጥ ይገባል ነው ያሉት። በዚህ ዓመት 31 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት መታረሱንም ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ በጥቅሉ 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ምርት መሠብሠቧን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘንድሮ ግን 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ኩንታል ምርት መሠብሠብ ተችሏል ነው ያሉት። ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 24 ነጥብ 7 በመቶ ዕድገት እንዳለውም ተናግረዋል። ዕድገቱ የተመዘገበው በመስኖ ልማት ሥራዎች እንደኾነም አንስተዋል።

እስከ መስከረም ባለው ጊዜም ስድስት ግድቦች እንደሚመረቁም ተናግረዋል። ለሜካናይዜሽንም ትኩረት መሠጠቱን ገልጸዋል። የሜካናይዜሽን ሥራው መስፋትም ለምርት እና ምርታማነት መጨመር አስተዋጽኦ እንዳደረገ ተናግረዋል። የበጋ ስንዴ ልማት ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱንም አመላክተዋል። በሌማት ትሩፋትም ለውጥ መገኘቱን ገልጸዋል።

የተገኙት ለውጦች እንደ መልካም ጅማሮ የሚወሰዱ እንጂ በቂ አለመኾናቸውን ነው የተናገሩት። የግብርናው ዘርፍ ትልቅ ትኩረት ያገኘ እና ትልቅ ውጤት ያመጣ እንደኾነም አመላክተዋል። ኢንዱስትሪው 12 ነጥብ 8 በመቶ ዕድገት እንዲያስመዘግብ ታስቦ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ታምርት በሚል ንቅናቄ ሰፊ ሥራዎች መከናዎናቸውንም አመላክተዋል። በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የማምረት አቅም 65 በመቶ መድረሱንም ተናግረዋል። የኢንዱስትሪ የኃይል ፍላጎት መጨመሩንም ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ታላላቅ የኢንዱስትሪ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውንም አመላክተዋል። የኢንዱስትሪ ዘርፉ በከፍተኛ መነቃቃት ላይ መኾኑንም አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ ታላቅ የማዕድን አቅም አላት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማዕድን ዘርፉ ትልቅ ለውጥ እየታየ ነው ብለዋል። በማዕድን ዘርፉ 3 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ለውጭ ገበያ መቅረቡንም አንሰተዋል። ብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ለማዕድን ዘርፍ ትኩረት ሰጥቷልም ነው ያሉት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየሰላም ግንባታ ጥረቶችን እና የልማት እንቅስቃሴዎችን ለማጠናከር ያለመ ምክክር በወግዲ ወረዳ ተካሄደ።
Next articleበዓመቱ 1 ነጥብ 3 ሚሊየን የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል።