
ባሕር ዳር: ሰኔ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት፣ 42ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ነው። በምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ.ር) ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ከሰጡባቸው ዘርፎች ውስጥ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው አንዱ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት በሀገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራቱ እንዲያንሰራራ፣ የግሉ ዘርፍን ለማነቃቃት፣ ምርታማነትን ለማሳደግ፣ በግብይት ሥርዓቱ የምጣኔ ሃብታዊ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙን መተግበር አሥፈልጓል።
ሪፎርሙ በኢትዮጵያ ተጀምሮ በኢትዮጵያ የሚያልቅ ሳይኾን ከዓለም ጋር ያለውን ትስስር ታሳቢ ያደረገ መኾኑን ነው የገለጹት። በተሠራው ሥራ ባለፈው ዓመት 8 ነጥብ 1 በመቶ እድገት መመዝገቡን ገልጸዋል። በዚህ ዓመትም 8 ነጥብ 4 በመቶ አጠቃላይ እድገት ለማስመዝገብ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ምንም እንኳ በዓለም ላይ ያለው ፈተና ዘርፈ ብዙ ቢኾንም የተቀመጠውን እቅድ ለማሳካት ከፍተኛ ትኩረት ተሠጥቶ እየተሠራ መኾን ነው ያነሱት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን