ከትምህርት ገበታ የራቁ ተማሪዎችን ለመመለስ ምን እየተሠራ ነው?

6

ባሕር ዳር: ሰኔ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት 42 መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ እና አስተያየት እያቀረቡ ነው።

የለውጡ መንግሥት የሰነበቱ የትምህርት ስብራቶችን ለመጠገን ሰፊ ሥራዎችን ጀምሯል፣ ነገር ግን አኹንም ብዙ ፈተናዎች የሚበዙት ነው ብለዋል። በተፈጥሮ እና በሠው ሠራሽ ችግሮች ከትምህርት ገበታ የራቁ ተማሪዎችን ለመመለስ ምን እየተሠራ እንደኾነም ጠይቀዋል።

የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን ላይ ማብራሪያ እንዲሰጥም አንስተዋል። በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል። የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ብዝኃ ዘርፍ በማድረግ ለውጥ እንዲመጣ ኾኗል ነው ያሉት። የሕዳሴ ግድብ ላይ የተወሰደው ቁርጠኛ አመራር እና ጽናት የሚደነቅ መኾኑንም ተናግረዋል።

በቱሪዝም፣ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የተሠራው ሥራ ጥሩ መኾኑን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄን በድፍረት ማንሳት እና በሰላማዊ መንገድ ለማገኘት እየተሄደበት ያለው አካሄድ ትልቅ መኾኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ ወዳጅ ሀገራት እያደረጉት ያለው ድጋፍ ምን እንደሚመስል ጠይቀዋል።የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብሩ የዲፕሎማሲ ሥራዎች ምን እንደሚመስሉ፣ በተለይም ከኤርትራ ጋር አኹን ላይ ያላት ግንኙነት ምን ይመስላል? የሚለው እንዲብራራላቸው አንስተዋል።

የመንግሥት የሠራተኞች እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ወገኖች የኑሮ ውድነትን መቋቋም እየቻሉ አለመኾኑን ገልጸዋል። የዜጎችን ጥያቄ ለመመለስ ምን እየተሠራ እንደኾነ አንስተዋል። የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ ጥረት ቢደረግም አኹንም የዋጋ ግሽበቱ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

በታጣቂ ኀይሎች የሚገደሉ ንጹሐንን መጠበቅ እንደሚባም አንስተዋል። ከታጣቂ ኃይሎች ጋር ችግሮችን በድርድር እና በውይይት ለመፍታት ምን እየተሠራ እንደኾነም ጠይቀዋል። የጸጥታ ችግሮችን መቅረፍ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት በመንገድ፣ በንጹሕ መጠጥ፣ በመስኖ እና በሌሎች የመሠረተ ልማት ሥራዎች መልካም ሥራዎች ተሠርተዋል ያሉት አባላቱ ነገር ግን አኹንም መፈታት የሚገባቸው ጥያቄዎች እንዳሉ አንስተዋል። የሕዝብ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች እንዲመለሱ በአዲሱ በጀት ዓመት ምን አይነት ዕቅድ እንደተያዘ እንዲብራራ ጠይቀዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየማክሮ ኢኮኖሚ አፈፃፀም በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጠየቁ።
Next article“8 ነጥብ 4 በመቶ አጠቃላይ እድገት ለማስመዝገብ እየተሠራ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ.ር)