
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት 6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት 42 መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው። በጉባኤው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ እና አስተያየት እያቀረቡም ነው።
ባለፉት ዓመታት በጦርነት ሥልጣን ለመያዝ በተደረጉ ግብግቦች ኢትዮጵያ ስትጎዳ መኖሩን ገልጸዋል። አሁንም ጦርነት የሚሰብቁ በርካታ አካላት መኖራቸውን አንስተዋል። የጦርነት ጎሳሚዎች ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
የጦርነት ጠማቂ ፖለቲከኞች መጋለጥ እንደሚገባቸው እና የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያወግዛቸው ማድረግ ይገባል ነው ያሉት። የፕሮቶሪያ ስምምነት በኢትዮጵያ ትልቅ ርምጃ ነው ያሉት አባላቱ አዲስ የፖለቲካ ባሕል መጀመሪያ መኾኑንም ገልጸዋል። ጦርነትን በማስቆም ሕዝቡ እፎይታ እንዲያገኝ አድርጓል፤ ነገር ግን የሕወሓት ጸብ አጫሪነት አሁንም አልቆመም ዳግም ግጭት እንደሚነሳም ስጋት አለ፣ መንግሥት ይሄን እንዴት እየተመለከተው ነው ብለዋል።
የግጭት መሠረታዊ ችግሮችን በመፍታት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች መልካም ውጤት እያሳዩ ይገኛሉ ያሉት አባላቱ ነገር ግን አሁንም በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ግጭት መኖሩን ተናግረዋል። ንጹሐንን የሚያግቱ እና የሚዘርፉ ጽንፈኞች መኖራቸውንም አንስተዋል።
ጽንፈኞችን ከሕዝብ በመነጠል አስተማማኝ ሰላምን ለማረጋገጥ ምን እየተሠራ እንደኾነም ጠይቀዋል።የመንግሥት ሠራተኞችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ምን እየተሠራ እንደኾነም አንስተዋል። በከተሞች እየታየ ያለውን የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመፍታት ምን እየተሠራ እንደኾነም ጠይቀዋል።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን