
ባሕርዳር: ሰኔ 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) በደቡብ ወሎ ዞን ከቦረና ወረዳ እና ከመካነ ሰላም ከተማ ነዋሪዎች ጋር በሰላም እና ልማት ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
በውይይቱ የደቡብ ወሎ ዞን ከፍተኛ የመንግሥት እና የጸጥታ ኀላፊዎችን ጨምሮ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች እና ሴቶች ተሳትፈዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች በታጣቂ ቡድኖች እየተፈጸመባቸው ያለውን አፈና፣ ዝርፊያ እና የኑሮ ውድነት ወደ ድህነት እየወሰዳቸው መኾኑን ገልጸዋል።
ከግለሰብ ሀብት እና ንብረት ዝርፊያ ባለፈ ጽንፈኛው ቡድን የሕዝብ መገልገያ ተቋማትን እያወደመ መኾኑንም የውይይቱ ተሳታፊዎች አስረድተዋል። የጽንፈኛውን ቡድን እኩይ ዓላማ እንደተረዱ እና ቡድኑን በመታገል የአካባቢያቸውን ሰላም ለመጠበቅ ከመንግሥት ጋር ተባብረው ለመሥራት ዝግጁ መኾናቸውን አረጋግጠዋል።
መንግሥት የመንገድ፣ የመብራት፣ የውኃ እና ሌሎች የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎቻቸውን እንዲመልስላቸውም ጠይቀዋል። እኛ አስፈላጊውን ዋጋ ከፍለን ሰላማችንን እናስጠብቃለን ያሉት ተሳታፊዎቹ መንግሥት ደግሞ የሚችለውን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ጥረት ያድርግ ብለዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮነን ማኅበረሰቡ ሰላሙን ማስከበር ከቻለ የሚነሱ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች በየደረጃው ለመመለስ እንደሚሠራ ገልጸዋል። ከማኅበረሰቡ ውስጥ ኾነው ለጥፋት ኀይሉ የስንቅ እና የመረጃ ድጋፍ እየሰጡ ያሉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።
ሕዝቡ ለመንግሥት እና ለጸጥታ መዋቅሩ ተባባሪ በመኾን ለአካባቢው ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የድርሻውን እንዲወጣ ነው የጠየቁት። የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) መንግሥት የግጭት መንስኤዎችን በመዋቅራዊ አደረጃጀት በመፍታት ለዘላቂ ሰላም እና ልማት መረጋገጥ በትኩረት እየሠራ መኾኑን አስረድተዋል።
መንግሥት ምንጊዜም ለሰላም አማራጭ ቅድሚያ እንደሚሰጥ ገልጸዋል። የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ታጣቂ ኀይሎች ወደ ሰላም እንዲመጡ እንዲሠሩም አሳስበዋል። ውይይቱ በቦረና ወረዳ እና በመካነ ሰላም ከተማ ያለውን የጸጥታ ሁኔታ ለማረጋጋት እና የሕዝቡን የልማት ጥያቄዎች ለመፍታት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ተመላክቷል። ኅብረተሰቡ ከመንግሥት ጋር በመተባበር ለመሥራት ያለው ዝግጁነት ለአካባቢው ዘላቂ ሰላም እና ልማት ወሳኝ ሚና እንደሚጫዎትም በመድረኩ ተገልጿል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን