
አዲስ አበባ: ሰኔ 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ የምግብ እና የመድኃኒት ባለሥልጣን የምግብ ደኅንነት እና ጥራት ቁጥጥር ከኢንሲ ናሽናል አክሪዲቴሽን ቦርድ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ማግኘቱን ገልጿል። እውቅናው በአምስት መለኪያዎች የተሰጠ መኾኑ ተመላክቷል።
ይህ ዕውቅና ባለሥልጣኑ በአዲስ አበባ ባካሄደው የምግብ ማምረቻ ቁጥጥር፣ ድህረ ግምገማ ክትትል፣ የመድኃኒት እና የሕክምና መሳሪያዎች ዕውቅና መርሐ ግብር ላይ ይፋ ተደርጓል።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ የኢትዮጵያ የምግብ እና የመድኃኒት ባለሥልጣን በአፍሪካ የምግብ እና የጤና ግብዓቶች ቁጥጥር የልህቀት ማዕከል የመኾን ራዕዩን ለማሳካት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸውን አሠራሮች በመከተል እየሠራ ነው ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት ባስፋፋው የጥራት አሥተዳደር ሥራዎች በርካታ ዕውቅናዎችን ማግኘቱን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ በቅርቡ በአምስት መለኪያዎች በምግብ አምራቾች ኢንስፔክሽን እና በድሕረ ገበያ ቁጥጥር የአይሶ 17020/2012 ዕውቅና እና የዓለም ጤና ድርጅት የቤንችማርክ ዕውቅና ማግኘቱን አብራርተዋል።
ከእነዚህም በተጨማሪ፣ የመድኃኒት ጥራት ምርመራ ላብራቶሪ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ የአይሶ 17025 ዕውቅናውን ማስቀጠል ችሏል። በ2022 በመድኃኒት ኢንስፔክሽን የአይሶ 17020 ዕውቅና፣ በ2023 ደግሞ የምግብ ጥራት ምርመራ ላብራቶሪ፣ የሕክምና ጓንት ጥራት ምርመራ፣ የሲሪንጅ ሁለት መለኪያዎች እና የፈጣን መመርመሪያ ኪት በአምስት መለኪያዎች አዲስ የአይሶ 17025/2017 ዕውቅና ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
ዋና ዳይሬክተሯ አዲሶቹንም ኾኑ ነባር ዕውቅናዎችን ማስቀጠል የጋራ ውጤት መኾኑን አንስተዋል። ባለሥልጣኑ ራሱን በተለያዩ ዓለም አቀፍ ደረጃዎች እና አሠራሮች በማሳደጉ በቀጣይ ለሚጠበቀው የምግብ እና የጤና ግብዓት ጥራት ደኅንነት ሥራ ትልቅ መሠረት መጣሉን ገልጸዋል። ይህ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ሀገሪቱ እየሠራች ላለው ውጤታማ የጤና ሥርዓት የተገኘው ዕውቅና ትልቅ ስኬት መኾኑን ገልጸዋል። በተለይም ባለሥልጣኑ የሚያካሂዳቸው የቁጥጥር ሥራዎች ለኅብረተሰቡ የሚቀርቡ የምግብ እና የጤና ግብዓቶች ጥራት፣ ደኅንነት እና ውጤታማነትን የሚያረጋግጡ በመኾናቸው ይህንን ሥራ በማጠናከር ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል። በመድረኩ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለነበራቸው አካላት ዕውቅና እና ሽልማት ተበርክቷል።
ዘጋቢ፦ ሰለሞን አሰፌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን