ሰላምን ለማጽናት በተካሄዱ ሰልፎች የወጣቶች እና የሴቶች ሚና ምን ነበር ?

20

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሰሞኑን በአማራ ክልል ሰላምን በመደገፍ ግጭትን በማውገዝ በተለያዩ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል።

በተካሄዱት ሰልፎች ወጣቶች እና ሴቶች በንቃት በመሳተፍ ስለ ሰላም ያላቸውን ፍላጎት ያሳዩባቸው እንደነበሩ ተገልጿል። በአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የወጣቶች ክንፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋሁን ተሰማ በክልሉ በተደረገው ግጭትን የማውገዝ እና ሰላምን የመደገፍ ሰልፍ ወጣቶች ግንባር ቀደም ኾነው መሳተፋቸውን አስታውቀዋል።

በዋናነት ወጣቶች ሲያስተላልፉት የነበረው መልዕክት ግጭት ይብቃን፣ ሰላምን፣ ልማትን እንፈልጋለን፣ የግጭቱ ተጎጅዎች እኛ ወጣቶች ነን፣ የሰላም ጥሪው መቀጠል አለበት የሚሉ ናቸው ብለዋል። ሰልፋ ሰላማዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅም ወጣቶች ሰፊ ሥራ መሥራታቸውንም አንስተዋል። ሰላሙ እንዲረጋገጥ ወጣቶች የራሳቸውን ሚና ለመጫወት ያላቸውን ቁርጠኝነትም አሳይተዋል ነው ያሉት።

ወጣቶች የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም አስቀጥለው ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ምክንያታዊ መኾን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። ወጣቶች ራስን ከግጭት በማራቅ እና በማኅበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ መልዕክቶችን አሰላስሎ በማየት ሰላሙን ዘላቂ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

በአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሴቶች ክንፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኢሌኒ ዓባይ ሴቶች ሰላምን መፈለጋቸውን በተካሄደው ሰልፍ ድምጻቸውን አሰምተዋል ነው ያሉት። የሴቶች ቁጥር አንድ ጥያቄ ሰላም ነው ያሉት ኀላፊዋ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነታችን የሚረጋገጠው ሰላም ሲኖር ነው ማለታቸውን ገልጸዋል።

አኹን በየአቅጣጫው እየገጠሙ ያሉትን ችግሮች ኹሉ መፍቻው መንገድ ሰላም መኾኑን ተናግረዋል። አኹን ለተገኘው ሰላም የሴቶች ሚና ከፍተኛ መኾኑንም አንስተዋል። በግጭት ማንም እንደማያተርፍ በቤተሰብ ደረጃ የምክክር አጀንዳ በማድረግ እናቶች እየሠሩ እንደኾነም ተናግረዋል።

ሰላምን አጀንዳ አድርገው በእድርም፣ በዕቁብም፣ በጽዋ ማኅበሩም የሚመክሩ የሰላም አምባሳደር እናቶች አሉ ነው ያሉት። ይህንንም አጠናክረው መቀጠል እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል። ሰላም እንዲመጣ ሁሉም ሴቶች ስለሰላም በመምከር የሚጠበቅባቸውን ማድረግ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ : አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleወባን የገቱ ጠንካራ እጆች እንዳይዝሉ።
Next articleየኢትዮጵያ ምግብ እና መድኃኒት ባለሥልጣን በአምስት መለኪያዎች አዲስ ዓለም አቀፍ ዕውቅና አገኘ።