
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ባለፈው ዓመት ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በወባ በሽታ ታመው ሕክምና አግኝተዋል፡፡ የበሽታውን ሥርጭት የመከላከል እና የመቆጣጠር ሥራ ለጤናው ዘርፍ ብቻ የማይተው በመኾኑ የክልሉ ማኅበረሰብ፣ ተቋማት እና አጋር ድርጅቶች የአካባቢ ቁጥጥር ሥራን አጠናክረው በትኩረት ሊሠሩ ይገባል፡፡
ወይዘሮ ሐመልማል ከተማ በባሕር ዳር ከተማ በዳግማዊ ምኒልክ ክፍለ ከተማ በሚገኝ አንድ ኮንዶሚኒየም ሕንጻ ውስጥ ይኖራሉ፡፡ እሳቸው እንደነገሩን አካባቢያቸው ረግረጋማ ነው፡፡ በመኾኑም በክረምት ያቆረው ውኃ በጋውን ሙሉ ይዘልቃል፡፡
ከየቤቱ ሚወጣው ፍሳሽ የሚወገደው በተዘጋጀ ጉድጓድ ውስጥ አልነበረም፡፡ ሁሉም ደጅ ላይ ይደፋል፡፡ ”በእንቅርት ላይ …” እንዲሉም በዝናብ ባቆረው ውኃ ላይ ፍሳሽ ሲጨመርበት ይበልጥ በአካባቢያቸው ኩሬ መፈጠሩን ወይዘሮ ሐመልማል አስታውሰዋል፡፡
በእነርሱ አካባቢም ሰርክ ከሕጻን እስከ አዋቂ በወባ በሸታ እንደሚጠቁ ነው የተናገሩት፡፡ በተከታታይ ቤተሰቦቻቸው በወባ የተጠቁባቸው አንዳንድ ሰዎችም ያቆረ ውኃን ለማፋሰስ ሲሞክሩ ሌላው የዳር ተመልካች ከመኾን ውጭ ‘ነግ በኔ’ ብሎ ባለማገዙ ውጤት ማምጣት አልተቻለም ብለዋል፡፡
ከጊዜ በኋላ ግን በዕለተ ዓርብ ጠዋት ዶማ፣ አካፋ… የያዘ ግብረ ኀይል አካባቢውን የማጽዳት፣ የማፋሰስ እና የማዳረቅ ሥራን ሲያከናውን መመልከታቸውን ተናግረዋል። ይህ መርሐ ግብርም ‘የዓርብ ጠንካራ እጆች የወባ ወረርሽኝን ይገታሉ’ በሚል መሪ መልዕክት የሚከወን ተግባር መኾኑን መገንዘባቸውንም ነው ያብራሩት፡፡
ወይዘሮ ሐመልማል እና ጎረቤቶቻቸው የግብረ ኀይሉን መልካም ሥራ በአርዓያነት ለማስቀጠል በመወሰን ዘወትር ዓርብ ጠዋት በመደበኛነት ማከናወን መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህም አካባቢያቸውን ማጽዳት እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡
ይሁን እና ‘የዓርብ ጠንካራ እጆች የወባ ወረርሽኝን ይገታሉ’ን የወል ሥራ ተከታትሎ የሚቆጣጠር አካል ባለመኖሩ አካባቢው ተመልሶ የውኃ ማቆሪያ ኾኗል ብለዋል፡፡ በባሕር ዳር ከተማ የፋሲሎ ከተማ ነዋሪው አቶ አዲሱ ሞገስ ”የዓርብ ጠንካራ እጆች የወባ ወረርሽኝን ይገታሉ” መርሐ ግብር በተጀመረ ማግስት በየሳምንቱ አካባቢያቸውን በተደራጀ መልኩ ያጸዱ እንደነበር ነግረውናል፡፡
ነገር ግን ሥራውን ከሦስት ሳምንት በላይ ማዝለቅ አለመቻላቸውን ጠቁመዋል፡፡ ሥራው ባለቤት ያስፈልገዋል ነው ያሉት፡፡ የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በድረ ገጹ ባሰፈረው መረጃ የክልሉ 80 በመቶ የሚኾነው የቆዳ ስፋት ለወባ መራቢያ ምቹ ነው፡፡
80 በመቶ የሚኾነው የክልሉ ሕዝብም ለወባ የተጋለጠ ነው፡፡ በ2016 በጀት ዓመት በክልሉ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የወባ ሕሙማን መመዝገቡ የበሽታውን ስፋት ያሳያል፡፡ በ2017 በጀት ዓመት እስከ ጥቅምት 10/2017 ዓ.ም ድረስ 696 ሺህ 325 የወባ ሕሙማን ተመዝግበዋል። ይህም ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 70 ነጥብ 5 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን መረጃው ጠቁሟል፡፡
በክልሉ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የወባ ፕሮግራም አስተባባሪ ዳምጤ ላንከር “የዓርብ ጠንካራ እጆች የወባ ወረርሽኝን ይገታሉ” በሚል መሪ መልዕክት ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል በማሳተፍ ክልላዊ ጤና ጣቢያ መር ማኅበረሰብ አቀፍ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ በዘመቻ ዘወትር አርብ ጠዋት ከ 1:00 እስከ 3:00 ከጥቅምት 15/2017 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ 2017 ዓ.ም መጨረሻ መተግበሩን ተናግረዋል፡፡
በዚህም በየደረጃው የሚገኙ መሪዎች እና ባለሙያዎች ቅንጅታዊ አሠራርን በማጠናከር የወባ ትንኝ መራቢያ ቦታዎችን በመለየት ማኅበረሰቡን በማሳተፍ ለወባ ትንኝ መራቢያ አመቺ የኾኑ ቦታዎችን የማጽዳት ሥራ ተከናውኗል፡፡
ዘመቻው በክልሉ ከፍተኛ የወባ ሥርጭት ያለባቸውን ሁሉንም ቀበሌዎች ተሳታፊ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል ነው ያሉት፡፡ በዚህም በየደረጃው የሚገኙ መሪዎች እና ባለሙያዎች ቅንጅታዊ አሠራርን በማጠናከር የወባ ትንኝ መራቢያ ቦታዎችን በመለየት የአካባቢ ቁጥጥር የማድረግ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት፡፡
መርሐ ግብሩ ሲጀመር በክልሉ በአንድ ሳምንት ብቻ 80ሺህ የሕሙማን ቁጥር በየሳምንቱ ይመዘገብ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በተሠራው ቅንጅታዊ ሥራ የሕሙማን ቁጥር እስከ 30ሺህ እንዲወርድ በማስቻል ጥሩ ውጤት ማስመዝገቡን ተናግረዋል፡፡
በአንጻሩ “የዓርብ ጠንካራ እጆች የወባ ወረርሽኝን ይገታሉ” የዘመቻ ሥራ ባይጀመር ኑሮ ሳምንታዊው የሕሙማን ቁጥር ከ80 ሺህ በላይ ይልቅ እንደነበር አስተባባሪው አብራርተዋል፡፡ በዘመቻ ሥራው ማኅበረሰቡ እንዲወጣ ቅስቀሳ መከናወኑን እና ክልላዊ የንቅናቄ መድረክ መዘጋጀቱን አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡
ይሁንና ሥራው ሲከናውን የሚሳተፈው የኅብረተሰብ ክፍል አነስተኛ ነበር ብለዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሰው ሥራው እና ችግሩን የኔ ነው ብሎ ባለመረዳት ለሌላው ሰው በመግፋቱ እንደኾነም ነው የጠቆሙት፡፡
የበሽታውን ሥርጭት የመከላከል እና የመቆጣጠር ሥራ ለጤናው ዘርፍ ብቻ የማይተው በመኾኑ የክልሉ ማኅበረሰብ፣ ተቋማት እና አጋር ድርጅቶች የአካባቢ ቁጥጥር ሥራን አጠናክረው በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ “የዓርብ ጠንካራ እጆች የወባ ወረርሽኝን ይገታሉ” የሚለው ሥራ ካለው ጠቀሜታ አንጻር ወደፊትም በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚሠራበት ነው አስተባባሪው የጠቆሙት፡፡
ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን