
ባሕር ዳር: ሰኔ 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሰላም ለአንድ አካል ብቻ እንደማይጠቅም ሁሉ በአንድ አካል ብቻ አይጠበቅም። ሰላምን የሚጠብቁት ሁሉም መኾን አለባቸው። ሁሉም ለሰላም ዘብ እስካልቆመ ድረስ የተሟላ ሰላም አይኖርም።
የተሟላ ሰላም በሌላ ጊዜ ደግሞ ወጥቶ መግባት፣ አርሶ መብላት፣ ነግዶ ማትረፍ፣ ልጆችን አስተምሮ ለቁም ነገር ማብቃት አይቻልም። ሰላም ለመኖር መሠረት ነው። ሰላም ካለ ሁሉም ነገር መልካም እየኾነ ይሄዳል። ሰላም ከሌለ ግን አኗኗር ሁሉ የከፋ ይኾናል።
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት እየተሠራ ነው። ነገር ግን እስካኹን ድረስ የተሟላ ሰላምን ማምጣት አልተቻለም። ብዙዎች ለሰላም ሢሠሩ ገሚሶች ደግሞ ሰላምን ለማደፍረስ ይሠራሉ።ሁሉም ለሰላም እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ስለ ሰላም መሥራት ካልቻለ የተሟላ እና ዘላቂ ሰላምን ማምጣት አይቻልም።
በሰላም ሚኒስቴር የግጭት ጥናት እና ትንተና ዴስክ ኀላፊ ይትባረክ ተስፋዬ የሰላም ሚኒስቴር ከተጡት ኀላፊነቶች መካከል የሰላም ግንባታ እና ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር ማድረግ ነው ብለዋል። ለሰላም ግንባታ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን የተናገሩት ኀላፊው የሃይማኖት አባቶችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ ልሂቃንን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እና ወጣቶችን በማወያየት የሰላም ግንባታ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል። ሁሉም ለሰላም የድርሻውን መወጣት አለበት ነው ያሉት።
ሰላም የአንድ አካል ብቻ እንዳልኾነ መረዳት እንደሚገባ፣ ለሰላም ሁሉም ዘብ መቆም እንዳለበት እና ችግሮች በንግግር እንዲፈቱ እየተሠራ ነው ብለዋል። ግጭቶች እንዳይከሰቱ በመከላከል ላይ የተመሠረተ ሥራ እንሠራለን ነው ያሉት ኀላፊው በግጭት ኹኔታ መከታተያ ክፍላቸው አማካኝነት ከየአካባቢዎች መረጃዎችን እንደሚሰበስቡ ተናግረዋል።
ችግሮች ሲገጥሙ በሚመለከተው አካል ምላሽ እንዲሰጥባቸው ተንትነን እናቀርባለን ነው ያሉት። በርካታ ችግሮች ወደ ሁከት እና ብጥብጥ ሳይሄዱ ለመፍታት ብዙ ጥረት መደረጉንም አንስተዋል። አንዳንድ ችግሮች ከአቅም በላይ ኾነው ግጭቶች ሲከሰቱ ግጭቶች እንዲቆሙ እንደሚሠሩም ተናግረዋል።
ግጭት ማስቆም ማለት ግጭት ማሥተዳደር ማለት ነው፣ ግጭት ማሥተዳደር ደግሞ ግጭቱን ማስቆም፣ ግጭቱ ወደ ሌላ እንዳይስፋፋ ማድረግ ነው ብለዋል። ግጭቶች በዘላቂነት እንዲፈቱ ባሕላዊ እሴቶችን እየተጠቀሙ እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል።
በግጭት አፈታት እና አሥተዳደር ሂደት የወጣቶች ሚና ከፍተኛ መኾኑንም ገልጸዋል። በተለይም እንደ ሀገር ወጣቶችን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማሳተፍ በርካታ ጥቅም እያስገኘ መኾኑን ነው የተናገሩት።
ወጣቶች ብልህ እና አስተዋይ መኾን አለባቸው ያሉት ኀላፊው ሀገር እና ወገን ሊጠቅም በሚችለው ጉዳይ ላይ መረባረብ አለባቸው ነው ያሉት። እንደ ሀገር የሚጠቅም ሥራ ላይ መሳተፍ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል። ከነፈሰበት ጋር መንፈስ አዋጭ እና ተገቢ አለመኾኑንም ገልጸዋል። የሰላም ሚኒስቴር የታነጸ ትውልድ እንዲፈጠር በትኩረት እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!