
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ፈለገ ሕይዎት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል “ፎር ዘወርልድ” ከተባለ ድርጅት ጋር በመተባበር ከሰኔ 23/2017 ዓ.ም ጀምሮ ነጻ የዐይን ሞራ ግርዶሽ የቀዶ ጥገና ሕክምና እየሰጠ ይገኛል፡፡
ሕክምናው እስከ ሰኔ 27/2017 ዓ.ም እንደሚቀጥል በሆስፒታሉ የዐይን ሕክምና ክፍል አሥተባባሪ ድረስ ዓለማየሁ ገልጸዋል። ለሕክምናውም እስከ 500 የሚደርሱ ሰዎች ተለይተዋል ብለዋል።
በሆስፒታሉ በተለይም ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን ከ12 ሺህ 500 በላይ ነጻ የዐይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ጥገና መሥራት መቻሉን ገልጸዋል። ከነጻ የሕክምና ዘመቻው በተጨማሪም በመደበኛ ሥራው ቢያንስ ከሳምንት ሁለት ጊዜ ከ20 በላይ የኾኑ ሰዎች አገልግሎቱን እያገኙ ነው፡፡
የዐይን ሞራ ግርዶሽ በኢትዮጵያም ኾነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለዐይነ ሥውርነት የሚያጋልጥ በሽታ ነው። በዘር፣ በዕድሜ፣ በአደጋ እና መሰል ምክንያቶች የሚከሰት እንደኾነ የተናገሩት አስተባባሪው በአብዛኛው ከ40 ዓመት በላይ የኾኑ ሰዎች የችግሩ ተጋላጭ መኾናቸውን ገልጸዋል። ችግሩ በቀላሉ መታከም የሚችል እንደኾነም አስገንዝበዋል። ቀዶ ጥገና ለችግሩ እንደ ዋና መፍትሔ ተደርጎ እንደሚወሰድም አመላክተዋል።
ዘጋቢ፡ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን