የኮምቦልቻ ከተማን ውበት የገለጠው የኮሪደር ልማት

18

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኮሪደር ልማት እንደሀገር የአዲስ አበባን ውበት በመግለጥ ወደ ክልል ከተሞች የተሻገረ ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው። የኮሪደር ልማት በአማራ ክልል ታላላቅ ከተሞችን ውበት እና የልማት ዐይን በመግለጥ የተጫዎተው ሚና ከፍተኛ ነው። የኮሪደር ልማት ሥራ ከተሞችን የማስዋብ እና የማዘመን ትልቅ ፕሮጀክት ነው፡፡

በኮሪደር ልማት ሥራ የከተሞች ጠባብ መንገዶች እንዲሰፉ ተደርገዋል፤ የተሽከርካሪ እና የእግረኛ መንገዶች ተለይተዋል፡፡ በመንገድ ላይ ሕገ ወጥ የኾኑ ለዕይታ እና ለእንቅስቃሴ ምቹ ያልኾኑ ሁኔታዎችን የመለወጥ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡

በአማራ ክልል የኮሪደር ልማት ሥራዎች በባሕር ዳር፣ በጎንደር፣ በደሴ፣ በኮምቦልቻ፣ በደብረ ብርሃን እና ሌሎች ከተሞች እየተሠራ ይገኛል፡፡ በኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር እየተሠራ ያለው ሥራ የከተማዋን ውበት ገልጧል። ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ጥቅምም ይዞ መጥቷል።

የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ነዋሪ አቶ እንድሪስ አህመድ በከተማዋ በሚሠራው የኮሪደር ልማት ደስተኛ መኾናቸውን ገልጸዋል። የኮሪደር ልማት በከተማዋ ላይ ለውጥ ያመጣ መኾኑንም ነግረውናል፡፡ የኮምቦልቻ ከተማ የዋና አስፋልት መንገድ ጠባብ፣ የተሽከርካሪ እና የእግረኛ መንገድ ያልተለየ፣ ለትራፊክ አደጋ የሚያጋልጥ ነበር ያሉት አቶ እንድሪስ አሁን ግን የእግረኞች፣ የተሽከርካሪ እና የብስክሌት መንገድ ተለይቶ ተሠርቷል ብለዋል፡፡

የኮሪደር ልማት በመሠራቱም ኅብረተሰቡ ከመኪና ጋር እየተጋፋ የመሄዱን ችግር አስቀርቶልናል፤ ልጆቻችን ይዘን የእግር ጉዞ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮልናል ነው ያሉት፡፡ በከተማዋ ከኮሪደር ልማት ሥራው በኋላ የተጀመሩ እና ቆመው የነበሩ ግንባታዎች እየተሠሩ ነው፤ ሥራ ያልጀመሩ ሆቴሎችም ሥራ ጀምረዋል ነው ያሉን፡፡

የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪው ወጣት አህመድ አብዱ በኮሪደር ልማቱ የሥራ ዕድል ተፈጥሮለት እየሠራ መኾኑን ተናግሯል፡፡ የኮሪደር ልማቱን በከተማዋ መሠረታዊ የሚባል ለውጥ እያመጣ መኾኑን አንስቷል፡፡

ሌላው በኮሪደር ልማት ሥራው የሥራ ዕድል ተጠቃሚ የኾነው ወጣት ጀማል መሐመድ ከጅማሬው ጀምሮ በአናጺ ሙያ እየሠራ ነው። እንደ እርሱ ሁሉ ለብዙ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ነው ያለው፡፡ በኮሪደር ልማት ሥራው ከገንዘብ ባለፈ የሙያ እና ክህሎት ልምድ እያገኙበት እንደኾነ ተናግሯል፡፡

መንገዶች ለማኅበረሰቡ ምቹ እንዲኾኑ በተለይም የአካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ተደርጎ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን አንስቷል፡፡ የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር መንገድ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አሥኪያጅ ሚኪያስ አሊ የኮሪደር ልማቱ የሰው እና የተሽከርካሪ መንገድ በመለየቱ በከተማዋ የነበረውን የትራፊክ መጨናነቅ እና አደጋውን በእጅጉ ቀንሶታል ብለዋል፡፡

በከተማውም ተሽከርካሪን ከመጠቀም ይልቅ ሰዎች በእግራቸው ለመጓዝ ምቹ ሁኔታ አግኝተዋል ነው ያሉት፡፡ በመሐል ከተማ የነበሩ ኮንቴነሮች እና የላስቲክ ቤቶች ተነስተው ከተማዋን ውብ፣ ጽዱ እና አረንጓዴ የማድረግ ሥራዎች መቀጠላቸውንም አብራርተዋል፡፡

የመንገድ መብራቶች በመኖራቸው ከውበት ባለፈ በምሽት ሰው እንደፈለገ እንዲንቀሳቀስ አድርጓል ያሉት ሥራ አሥኪያጁ የመንገድ መብራቶች እና ከተማዋን ስማርት ሲቲ ለማድረግ በዋና ዋና ጎዳናዎች የተገጠሙ የመንገድ ላይ ካሜራዎች የጸጥታ ሁኔታውን ለማሻሻል ዕድል ፈጥረዋል ነው ያሉት፡፡ በሚሠሩ ሥራዎችም የቴክኖሎጅ ዕውቀት እንዲዳብር ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡

በከተማዋ ለሚገኙ የኮንስትራክሽን ግብዓት አቅራቢዎች፣ ማሽን አከራዮች እና ሌሎች የሙያ እና ጉልበት ሠራተኞች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ነው ያሉት፡፡ በከተማዋ የሚገኙ የንግድ እንቅስቃሴዎችን እና ኢንቨስትመንቱን ማነቃቃት የተቻለበት ሥራ ነው ያሉት ዋና ሥራ አሥኪያጁ ሆቴሎች እና ሌሎች አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ተነቃቅተው እየሠሩ ነው ብለዋል፡፡

የኮሪደር ልማት በተሠራባቸው ቦታዎች ተጀምረው ያላለቁ እና ግንባታቸው ቁመው የነበሩ ወደ ግንባታ ገብተዋል፤ ግንባታ ያጠናቀቁትም አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን አንስተዋል፡፡ በሆቴል ኢንቨስተመንት ዘርፉም ባለሃብቶች በከተማዋ በርካታ ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡ በኮሪደር ልማት ሥራው ኅብረተሰቡ ደስተኛ መኾኑን በሚሰጣቸው ድጋፍ ማረጋገጣቸውን የሚናገሩት ሥራ አሥኪያጁ እስካሁን ምንም አይነት ችግር እንዳልገጠማቸው ነው የተናገሩት፡፡

ዘጋቢ፡ ፍሬሕይወት አዘዘው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleምክትል ርእሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) በመካነ ሰላም ከተማ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር እየተወያዩ ነው።
Next articleፈለገ ሕይዎት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ነጻ የዐይን ሞራ ግርዶሽ የቀዶ ጥገና ሕክምና እየሰጠ ነው።