
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ደም መለገስ በፍላጎት ወይም በፈቃደኝነት ላይ ተመስርቶ የሚደረግ በጎ ተግባር ነው፡፡
በጎ ፈቃደኞች ደም ለመስጠት ተስማምተው ከለገሱ በኋላ ደሙ ለሌላ ደም ለሚያስፈልገው ግለሰብ ይለገሳል፡፡ በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሌላ ሰው ደም ይፈልጋሉና። አንዳንዶቹ በቀዶ ጥገና ጊዜ ደም ይፈልጋሉ። ሌሎቹ ደግሞ ከአደጋ በኋላ ወይም የውስጥ ደዌ ችግር ሲጋጥማቸው ደም ይለገሳሉ፡፡
ደም መለገስ እነዚህን እና ሌሎችንም ችግሮች ይፈታል፡፡ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዋ ፍሬሕይወት ሙስጦፋ “በአንድ ወቅት በባሕርዳር ፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በሄድኩበት አጋጣሚ ከገጠር የመጣች ነፍሰ ጡር እናት ደም እንደሚያስፈልጋት ተመለከትኩ። ደም የሚሰጣት ስታጣም አየሁ። በፍላጎት እኔ ሰጠኋት፤ በዚህም ነፍሰጡሯ በሰላም ተገላገለች። በሙሉ ጤንነቷ በማየቴ እና ከፈጣሪ በታች ለሰዎች መዳን ምክንያት በመኾኔ የተሰማኝ ደስታ ወደር አልነበረውም” ነው ያሉን ደም በመለገስ ያገኙትን ሀሴት ሲነግሩን።
ይህም አጋጣሚ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ በቋሚነት ደም እንዲለግሱ ምክንያት እንደኾናቸው ተናግረዋል። ወይዘሮ ፍሬሕይዎት ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ለ41 ጊዜ ደም መለገስ መቻላቸውን ነግረውናል፡፡
የባሕር ዳር ደም ባንክ ኀላፊ ምክሩ ሽፈራው የባሕር ዳር ደም ባንክ በ2017 በጀት ዓመት 25 ሺህ ከረጢት ደም በመሠብሠብ በሰላሳ አራት የግል እና የመንግሥት ሆስፒታሎች ለማሠራጨት ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል። በዚህም ከዕቅዱ 101 በመቶ የሚኾነውን ደም በመሠብሠብ ማሠራጨት መቻሉን ተናግረዋል።
የተሠራጨው ደም ለ24 ሺህ ደም ፈላጊ ታካሚዎች ግልጋሎት ላይ ሊውል እንደሚችል የተናገሩት ኀላፊው እስካሁንም 15 ሺህ ደም ፈላጊ ታካሚዎች ተጠቃሚ ኾነዋል ብለዋል። አብዛኛዎቹ ደም ለጋሾች ወጣቶች በመኾናቸው በትምህርት ቤቶች፣ በዩንቨርሲቲዎች እና በኮሌጆች ደም እንዴት እንደሚሠበሠብ፣ የት ሆስፒታል እንደሚሠራጭ፣ ለምን አይነት ታካሚዎች ደም እንደሚሰጥ ተከታታይነት ያለው ትምህርት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
ደም ለጋሽ ወጣቶች ባይኖሩ ደም በሚያስፈልገው ታካሚ ላይ ምን ሊከሰት እንደሚችል በማሳየት ከፍተኛ የንቅናቄ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት። ወጣቶቹ ከራሳቸው አልፈው ቤተሰቦቻቸውን፣ የአካባቢያቸውን ማኅበረሰብ በማስተባበር እና በማሳመን የዚህ በጎ ተግባር ተሳታፊ እንዲኾኑ በማድረግ በክረምት ወቅት ሊያጋጥም የሚችለውን የደም ልገሳ እጥረት ለመቅረፍ የቅድመ ደም ሥብሠባ ሥራ መሠራቱም ተናግረዋል።
የባሕር ዳር ደም ባንክ በሥራው በኢትዮጵያ ቀዳሚ በመኾን ለሰባት ተከታታይ ዓመታት ተሸላሚ መኾኑንም ጠቁመዋል።ማኅበረሰቡ ለደም ልገሳ በጎ ፈቃደኝነት ተባባሪ መኾኑን አሳይቷል ብለዋል።ደም መለገስ የውዴታ ግዴታ እንደኾነ ለማኅበረሰቡ በስፋት በማስተማር፣ ግንዛቤ በመፍጠር ከዚህ በበለጠ የደም ለጋሽ ቁጥሮችን የማብዛት እና ደም የሚያስፈልጋቸውን ታካሚዎች ደም በመለገስ ሕይወታቸውን ለመታደግ በትጋት እንደሚሠሩ አብራርተዋል፡፡
ደም ለየትኛውም አካል አገልግሎት የሚውል በመኾኑ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ኾነን ደም በመለገስ ሀገራዊ ፍቅራችንን እና ወገናዊ አለኝታነታችን እንወጣ ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ፍጹም ሰበዓዊ ከኾነው አገልግሎት ዋነኛው እና ቀዳሚው አገልግሎት ደም መለገስ መኾኑንም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን