
ደብረማርቆስ፡ ሰኔ 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ማርቆስ ከተማ የተካሄደው ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ኅብረተሰቡ ከተማ አሥተዳደሩ እያከናወናቸው ለሚገኙ የልማት ሥራዎች ዕውቅና የሰጠበት እና ለሰላም ያለውን ጽኑ አቋም ያሳየበትእንደነበር የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ ገልጸዋል፡፡
ኅብረተሰቡ በሰላማዊ ሰልፍ የጠየቃቸውን የሰላም የመልካም አሥተዳደር እና የልማት ጥያቄዎችን እንደ ግብዓት በመውሰድ ከተማ አሥተዳደሩ በትኩረት እንደሚሠራባቸው ተናግረዋል። ከተማ አሥተዳደሩ በአጭር ጊዜ ለሚፈቱ ችግሮች ትኩረት በመስጠት የ90 ቀናት ዕቅድ አቅዶ ወደ ሥራ መግባቱንም ጠቁመዋል፡፡
የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ ማድረግ የመሪው ግንባር ቀደም ተግባር መኾኑንም መግባባት ላይ ተደርሷል ነው ያሉት፡፡ኅብረተሰቡን የሰላሙ ባለቤት ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎችን ለማጠናከር ከተማ አሥተዳደሩ አበክሮ ይሠራል ብለዋል።
የሰላም አማራጭን ተከትለው ለሚመጡ ታጣቂ ኀይሎች በሩ ክፍት ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ችግሮችን በንግግር ለመፍታትም ጥረት ይደረጋል ነው ያሉት። ሰላማዊ መንገድን ተከትለው ለሚገቡ ታጣቂዎች የማቋቋም እና ሕጋዊ በኾነ መንገድ ኅብረተሰቡን እንዲቀላቀሉ ለማደረግ ይሠራል ብለዋል።
ኅብረተሰቡ እየደረሰበት ያለውን የማኅበራዊ እንቅስቃሴ መገደብ፣ እንግልት እና ሕገ ወጥነትን ለመከላከል የተጀመሩ ሕግ የማስከበር ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመላክተዋል፡፡ኅብረተሰቡን ተሳታፊ በማድረግ የተጀመሩ የልማት ሥራች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የተናገሩት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የክረምት አረንጓዴ ልማት ሥራዎችን ጨምሮ ሌሎችንም ተግባራት ለመፈጸም ታቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
የተቋም ግንባታ፣ የሰው ኀይል ሪፎርም ሥራዎች እና ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ አገልግሎት አሠጣጥ በትኩረት እየተሠራባቸው እንደኾነም ገልጸዋል፡፡ የተገልጋዮችን እንግልት ለማስቀረት እና የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት ከከንቲባ እስከ ቀበሌ ድረስ የተገልጋይ ቀን በመዘርጋት ወደ ተግባር ተገብቷል ተብሏል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን