“የጸጥታ መዋቅሩን በማጠናከር የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሠራ ነው” አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

23

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት መሪዎች እና የክልሉ የጸጥታ ኀላፊዎች በደቡብ ወሎ ዞን ለጋምቦ ወረዳ የአካባቢያቸውን ሰላም እያረጋገጡ ያሉ የሰላም አስከባሪ እና ሚሊሻ አባላትን በቦታው ተገኝተው አበረታተዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) በክልሉ እየታየ ያለውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ተሟላ ሰላም ለመለወጥ የክልሉን የጸጥታ መዋቅር ለማጠናከር በልዩ ትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።

የጸጥታ መዋቅሩ በመጠናከሩ ከምንጊዜውም በላይ የክልሉ ሰላም እየተሻሻለ እና ማኅበረሰቡ የሚያነሳቸው የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ዕድል መፍጠሩን ነው ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ የተናገሩት።

የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ሀገር በቀል ዕውቀታቸውን እና አቅማቸውን ተጠቅመው በተሳሳተ ዓላማ የተሰለፉ ኃይሎች የሰላምን አማራጭ እንዲከተሉ አበክረው መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን የጸጥታ መዋቅሩን ማጠናከር በመቻሉ እና የዞኑ ማኅበረሰብ የጽንፈኛውን እኩይ ዓላማ በመረዳቱ ዞኑ ወደ ተሟላ ሰላም እየገባ ነው ብለዋል። ለአሚኮ አስተያየት የሰጡ የሚሊሻ አባላት በበኩላቸው ታጣቂ ቡድኑ በእየዕለቱ እያደረሰ ባለው ግፍ እና መከራ አካባቢያቸውን ተደራጅተው ለመጠበቅ እንዳስገደዳቸው ነው የተናገሩት።

ታጣቂ ቡድኑ መንግሥት እና ሕዝብ እያቀረበለት ያለውን ተደጋጋሚ የሰላም አማራጭ መቀበል አለበት ያሉት የሚሊሻ አባላቱ ከዚህ ውጭ ያለውን ኃይል ግን ካለው የጸጥታ መዋቅር ጋር በመቀናጀት ሕግ እንደሚያስከብሩ ተናግረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleምክር ቤቱ የዲጂታል አሠራርን በመተግበር ለሌሎች ተቋማት አርዓያ መኾን እንዳለበት የቋሚ ኮሚቴ አባላት አሳሰቡ።
Next articleኅብረተሰቡ በሰላማዊ ሰልፍ የጠየቃቸውን የሰላም እና የልማት ጥያቄዎች ለመፍታት በትኩረት ይሠራል።