ምክር ቤቱ የዲጂታል አሠራርን በመተግበር ለሌሎች ተቋማት አርዓያ መኾን እንዳለበት የቋሚ ኮሚቴ አባላት አሳሰቡ።

11

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የመንግሥት ወጭ አሥተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የክልሉን ምክር ቤት የኦዲት ግኝት ምላሽ ገምግሟል። በግምገማው ከ2009 እስከ 2014 ዓ.ም በዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የተገኙ የኦዲት ግኝቶች፣ በተወሰደው ርምጃ እና የምላሽ አሰጣጥ ሂደት በተመለከተ በምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት በኩል ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በውይይቱ በቋሚ ኮሚቴው አባላት እና በኦዲተሮች የተለያዩ ሀሳቦች እና አስተያየቶች ተነስተዋል።ተቋሙ ርምጃ የወሰደባቸውን የኦዲት ግኝቶች መረጃ በአግባቡ ማቅረብ አለመቻሉ፣ በንብረት አመዘጋገብ፣ አያያዝ እና አሥተዳደር ላይ ክፍተቶች መኖራቸው በቋሚ ኮሚቴው አባላት ተነስተዋል።

የተሠብሣቢ እና ተከፋይ ሒሳቦች ክምችታቸው ከዓመት ዓመት እየጨመረ መምጣቱ፣ ለተደረገው የኦዲት ግኝት ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ትኩረት አለማድረግ፣ ሂሳቦችን በማስረጃ ያለማቅረብ ችግሮች መኖራቸው በቋሚ ኮሚቴው ተገምግሟል።

የንብረት አመዘጋገብ፣ አሥተዳደር እና መረጃ አያያዝ ላይ ክፍተቶች የሚስተዋሉ መኾኑንም የቋሚ ኮሚቴው አባላት ጠቁመዋል። የግዥ ሥርዓቱን በተመለከተ ሰነድ በማሟላት ሕጋዊ እያደረጉ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ምክር ቤቱ የሒሳብ አያያዝንም ኾነ የንብረት አሥተዳደርን የዲጅታላይዝ አሠራር በመተግበር ለሌላው ተቋም አርዓያ መኾን እንዳለበት ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።በአማራ ክልል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ምክትል ዋና ኦዲተር ሰውበሰው ብዙአየሁ በተገኙት ግኝቶች በተደጋጋሚ የማሥተካከያ ርምጃዎች እንዲወሰድ ውይይቶች ተደርገው አስተያየት ተሰጥቷል ብለዋል።

ይህንን ተከትሎ ግኝቶች እንዴት እንደተስተካከሉ አጥጋቢ መረጃ ከማቅረብ አንጻር ውስንነቶች እንዳሉ ጠቁመዋል። ከተከፋይ ሂሳብ አንፃርም ጥንቃቄ በማድረግ ተቋሙ ማየት እንደሚገባው አመላክተዋል።

ከቀጥታ ግዥ ጋር የሚያጋጥሙ ችግሮችን በተመለከተ አስገዳጅ ኾነው ሲገኙ ለሦስተኛ ወገን ግልጽ በኾነ እና ለኦዲተር በሚመች መንገድ ማከናወን ይገባል ነው ያሉት።የአማራ ክልል ምክር ቤት የመንግሥት ወጭ አሥተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ እመቤት ከበደ መረጃ አያያዝ እና አጠቃቀም ላይ ኦዲተር በሚፈልገው መልኩ በግልጽ ማቅረብ ይጠበቃል ብለዋል።

ንብረት ክፍል በፊት በተሰጠው ድጋፍ እና አስተያየት መሠረት መሻሻሎች ስለመታየታቸው አስገንዝበዋል። በወቅቱ መወገድ ያለባቸውን ንብረቶች ማስወገድ እና አገልግሎት የሚሰጡትንም ማሠራጨት ይገባል ነው ያሉት።

ንብረት አያያዝ እና አመዘጋገብ ላይ ዘመናዊነትን በመከተል ወደ ዲጂታላይዜሽን ለመምጣት ተቋሙ በትኩረት መሥራት እንደሚገባው አሳስበዋል። ዘመኑን የዋጀ ሥልጠና እና ግንዛቤ ለባለሙያዎች መስጠት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት ጽሕፈት ቤቱ ኀላፊ ሀይሌ ብርሀን ቋሚ ኮሚቴው በሰጠው አቅጣጫ መሠረት አስተያየቶችን ወስዶ የማሥተካከል ሥራ እንደሚሠራ ገልጸዋል። ንብረት አወጋገድን በተመለከተ በርካታ ንብረቶችን አሠራሩን ጠብቀው መወገዳቸውን አንስተዋል።

በቀጣይም ሳይንሳዊ በኾነ መንገድ የንብረት አያያዝ ሥርዓትን በመከተል እንደሚሠራ አመላክተዋል። የሂሳብ አያያዝ እና አጠቃቀም ላይ መረጃዎችን በዝርዝር በመገምገም በቀጣይ ምላሽ እና ማብራሪያ ይሰጣል ነው ያሉት።

ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበአውሮፓ ኅብረት ድጋፍ የሚከናወን የአደጋ ተጋላጭነት ቅነሳ ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ።
Next article“የጸጥታ መዋቅሩን በማጠናከር የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሠራ ነው” አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)