በአውሮፓ ኅብረት ድጋፍ የሚከናወን የአደጋ ተጋላጭነት ቅነሳ ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ።

14

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ከአውሮፓ ኅብረት ያልተማከለ የአደጋ ስጋት ቅነሳ አሥተዳደር በኢትዮጵያ ጋር የሁለተኛ ዙር ፕሮጀክት እወጃ ዙሪያ ውይይት አድርጓል።

በውይይቱ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሰርካዲስ አታሌ ላለፉት 30 ዓመታት አደጋ ከደረሰ በኋላ እርዳታ የማቅረብ እና የመከላከል ሥራ ሲከናወን መቆየቱን ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ የአደጋ መንስኤውን ቀድሞ በማወቅ፣ በመከላከል እና በመቀነስ ላይ የተመሠረተ የአደጋ ስጋት አመራር እየተከናወነ መኾኑን ገልጸዋል።የሕዝብን የአደጋ ተጋላጭነት ለመቀነስ እና የመቋቋም አቅምን ከፍ ለማድረግ ታሳቢ ያደረጉ ፕሮጀክቶች ሲፈጸሙ መቆየታቸውን ተናግረዋል። ከእነዚህ ውስጥም በአውሮፓ ኅብረት የገንዘብ ድጋፍ ለአምስት ዓመታት ሲከናወን የቆየው ያልተማከለ የአደጋ ስጋት ቅነሳ አሥተዳደር ችግሮችን ሲፈታ መቆየቱን ገልጸዋል።

የአደጋ ስጋት ተጋላጭነትን በመለየት፣ ጥናት በማድረግ ፣ በማቀድ መሥራት እና በቀውስ ጊዜ ምላሽ በመስጠት ሲሠራ የቆየው ይሄው ፕሮጀክት ሁለተኛውን ዙር ለማጽደቅ መወያየታቸውን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ ከበፊቱ አፈጻጸሞቹ ልምድ በመውሰድ ለችግሮች በተለይም ለፕሮፋይል ጥናት ዝግጅት ዕቅድ እና ትግበራ ትኩረት በመስጠት እና የቅድመ ማስጠንቀቂያን በማዘመን ለኦቶሜሽን ሥራዎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል ብለዋል።

የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ሊዘምን የሚችለው በወረዳ አደጋ ስጋት ፕሮፋይል ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሯ ሁሉም ምላሾች ለቅድመ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ሥርዓት ግንባታ እና ለአደጋ ተጋላጭነት ምላሽ ዝግጅት ወሳኝ ናቸው ብለዋል።ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ዙር አፈጻጸምን በመገምገም እጥረቶችን ለማስተካከል እና ጥንካሬዎችን ለማስቀጠል እንደሚሠራም ገልጸዋል። ፕሮጀክቱን ለማዘጋጀት ትብብር ያደረጉትን ሁሉ አመስግነዋል። ኮሚሽናቸው ፕሮጀክቱን በመከታተል ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።

በአማራ ክልል የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን በአውሮፓ ኅብረት ድጋፍ ያልተማከለ የአደጋ ሥጋት ቅነሣ ሥራ አመራርን የማጠናከር ፕሮጀክት ሥራ አሥኪያጅ አዝመራው ምንላርግህ ከዚህ በፊት እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ያለውን ክፍተት ለይቶ የአቅም ግንባታ ሥራ እንደተሠራ ገልጸዋል።

የአደጋ ሥጋት ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ሥራዎች ሲተገበሩ መቆየታቸውንም ጠቅሰዋል።በሁለተኛ ዙር ፕሮጀክትም ካለፈው በመማር ተጠናክሮ እንደሚፈጸም እና በመረጃ ላይ የተመሠረተ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ሥራ እንደሚሠራ ነው የገለጹት።

በኮሚሽኑ የአውሮፓ ኅብረት ፕሮጀክት ቴክኒካል አማካሪ አያጣም ፈንታሁን ፕሮጀክቱ ገንዘቡ ወደ መንግሥት ካዝና ገብቶ መንግሥት በራሱ የችግር ልየታ እና መፍትሔ አፈላለግ ላይ ሙያዊ ድጋፍ እየተደረገለት የሚፈጸም መኾኑን ገልጸዋል።

ኅብረተሰቡን ለአደጋ የማይበገር ለማድረግ የዳሰሳ ጥናት በማድረግ የሚሠራ ፕሮጀክት መኾኑንም ተናግረዋል። ከማኅበረሰብ እስከ ቤተሰብ ድረስ የተለያዩ የተጋላጭነት ቅነሳ እና የአይበገሬነት አቅም ግንባታ ሥራዎች እንደሚሠራም ጠቅሰዋል።

ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበ25 ከተሞች አዲስ የባንክ አካውንት ለመክፈት የፋይዳ ዲጅታል መታወቂያ አስገዳጅ ኾነ።
Next articleምክር ቤቱ የዲጂታል አሠራርን በመተግበር ለሌሎች ተቋማት አርዓያ መኾን እንዳለበት የቋሚ ኮሚቴ አባላት አሳሰቡ።