በ25 ከተሞች አዲስ የባንክ አካውንት ለመክፈት የፋይዳ ዲጅታል መታወቂያ አስገዳጅ ኾነ።

30

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በ25 ከተሞች አዲስ የባንክ አካውንት ለመክፈት የፋይዳ ዲጅታል መታወቂያ አስገዳጅ መኾኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

ከሰኔ 24/2017 ዓ.ም ጀምሮ በሀገሪቱ በሚገኙ 25 ከተሞች አዲስ የባንክ ሒሳብ ለመክፈት የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ እንደ መጀመሪያ ቅድመ ሁኔታ ተግባራዊ መኾኑን በጽሕፈት ቤቱ የስትራቴጅክ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቤኔዘር ፈለቀ ገልጸዋል።

አሠራሩ በሁሉም ባንኮች ተግባራዊ እንደሚኾን ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት። በአማራ ክልል ባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ ደሴ፣ ደብረ ብርሃን እና ኮምቦልቻ ተግባራዊ የተደረገባቸው ከተሞች ኾነዋል። በቀጣይ በሌሎች የክልል ከተሞች ይተገበራል ብለዋል። ነባር የባንክ አካውንት ያላቸውን ተገልጋዮች የፋይዳ ዲጅታል መታወቂያ ከባንክ የሂሳብ ቁጥራቸው ጋር ማስተሳሰር የሚያችል ሥርዓት እየተዘረጋ መኾኑንም ገልጸዋል።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት እስካሁን ከ18 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የፋይዳ ዲጅታል መታወቂያ ተጠቃሚ ኾነዋል። በቀጣይ ሁለት ዓመታት ከ70 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተደራሽ ለማድረግ በሀገሪቱ ከ1 ሺህ በላይ የምዝገባ ጣብያዎችን በማቋቋም የፋይዳ ዲጅታል መታወቂያ ምዝገባ እየተካሄደ መኾኑን ገልጸዋል።

ማንኛውም ሰው ሕጋዊ ማንነቱን የሚገልጽ ማንኛውንም ማስረጃ በመያዝ በአቅራቢያው በሚገኝ የኢትዮ ቴሌኮም ማዕከል ወይንም የገቢዎች ቢሮ መመዝገብ እንደሚችል አንስተዋል። የዲጅታል መታወቂያ ፋይዳ መሠረታዊ ማንነትን የሚለይ፣ ማንኛውንም ሰው በየትኛውም አካባቢ የዲጅታል መታወቂያ ባለቤት የሚያደርግ፣ ለኢትዮጵያ ዜጋ ብቻ ሳይኾን በሀገሪቱ ውስጥ የኑሮ ወይም የሥራ ፈቃድ ያለውን ማንኛውም ሕጋዊ ነዋሪ (የውጭ ዜጎችን ጨምሮ) ተጠቃሚ የሚያደርግ ብሔራዊ መታወቂያ ነው።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) በመካነ ሰላም ከተማ የሚገነቡ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ጎበኙ።
Next articleበአውሮፓ ኅብረት ድጋፍ የሚከናወን የአደጋ ተጋላጭነት ቅነሳ ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ።