የኦፓል ልማት ዘርፉ ከአመራረት እስከ ግብይት ሂደት ውስብስብ ችግሮች አሉበት።

20

ደሴ: ሰኔ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን፣ የአማራ ክልል ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ፣ ወሎ ዩኒቨርሲቲ እና ባለድርሻ አካላት በምክክር መድረኩ ተሳትፈዋል፡፡

የኦፓል ማዕድን በአማራ ክልል በስፋት የሚገኝ መኾኑን ያነሱት የክልሉ ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ ኀላፊ ኃይሌ አበበ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እና ተመራጭ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ከአመራረት እስከ ግብይት ሂደት ዘርፉ ውስብስብ ችግሮች እንዳሉበትም ገልጸዋል፡፡ እንደ ማዕድኑ ተፈላጊነት እና ብዛትም ከዘርፉ በሚገባን ልክ ተጠቃሚ መኾን አልተቻለም ነው ያሉት ቢሮ ኀላፊው፡፡

የአመራረት ዘመናዊነት መጓደል፣ የገበያ ትስስር ችግር፣ ሕገወጥነት እና ኮንትሮባንድ እንዲሁም የፋይናንስ አቅርቦት አለመኖር የዘርፉ ሁነኛ ችግሮች መኾናቸውን ቢሮ ኀላፊው አመላክተዋል፡፡የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብስራት ከበደ (ዶ.ር) በኦፓል ማዕድን ልማት ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ስትራቴጂ መዘጋጀቱን እና ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል፡፡

በዘርፉ የሚስተዋለውን የክህሎት ማነስ፣ ከአመራረት ጀምሮ የምርት ብክነት፣ እሴት የመጨመር ውስንነት እንደሚታይ በጥናት ተረጋግጧል ብለዋል፡፡የዘርፉ ፈተና የኾነው ባሕላዊ የግብይት ሥርዓት መኾኑን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ ችግሩን ለመፍታት ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን ጋር እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን የስትራቴጂክ ክፍል ኀላፊ ባየልኝ ዘርዓይ የኦፓል ምርትን ለዓለም ገበያ አምራች እና ሻጭ በመኾን አውስትራሊያ ቀዳሚ መኾኗን አንስተዋል፡፡ ይህ የኾነበት ምክንያትም የተደራጀ የገበያ ሥርዓት በመዘርጋታቸው ነው ብለዋል፡፡

በመኾኑም እንደ ሀገር የምርት ሂደቱን እና የገበያ ሥርዓቱን የሚያመላክት ዘመናዊ አሠራር ለመተግበር በጋራ ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡በወሎ ዩኒቨርሲቲ የኢንዱስትሪ ዩኒቨርሲቲ ትስስር እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር አሳምን አያሌው (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው በኦፓል ማዕድን ላይ የተለያዩ ምርምሮችን ከመሥራት ባሻገር በቴክኖሎጂ እና በብቁ የሰው ኃይል ዘርፉን ለማገዝ ሥራዎችን በትኩረት በመሥራት ላይ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

እሴት ጨምሮ ለገበያ ለማቅረብ የሚያስችል የመቁረጫ ማሽን፣ በቁፋሮ ሂደት ሊወገድ የሚችል አፈርን ለማንሳት የሚያስችል ቴክኖሎጂ እየሠሩ መኾናቸውንም ዶክተር አሳምን አንስተዋል፡፡ በመድረኩ በኦፓል ማዕድን የአመራረት ሂደት እና ግብይት ላይ የሚስተዋሉ ውስንነቶች እና የመፍትሄ ሃሳብ የሚያመላክቱ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ጀማል ይማም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleቱሪዝሙን ለማነቃቃት ሁሉም ተቋማት የየራሳቸው ድርሻ ይወጡ።
Next articleምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) በመካነ ሰላም ከተማ የሚገነቡ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ጎበኙ።