
ባሕር ዳር: ሰኔ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ጎጃም ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ በዞኑ ያለውን የቱሪዝም ሃብት የማስተዋወቅ አውደ ርዕይ እና የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት የማቋቋም የውይይት መድረክ አካሂዷል።
የቱሪዝም ሃብቶችን ማስተዋወቅ እና የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ማቋቋም ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመኾን ያስችላል ተብሏል። የሰሜን ጎጃም ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ምትኬ ባዩ በሰሜን ጎጃም ዞን በርካታ የቱሪዝም ጸጋዎች መኖራቸውን ገልጸዋል። ጸጋዎችን አልምቶ እና ተንከባክቦ ጎብኝዎችን ለመሳብ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ታሪካዊ ቅርሶችን የመንከባከብ፣ የማደስ፣ ተፈጥሯዊ ሥፍራዎችን የማልማት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ነው ያነሱት። የተቋቋመው የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ተቋማትን አቀናጅቶ ለማሠራት እና በዘርፉ ውጤታማ ለመኾን ያስችላል ነው ያሉት።
የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤቱ ተቋማትን አቅፎ የያዘ መኾኑን ተናግረዋል። ቱሪዝም ብቻውን ውጤታማ ሥራ መሥራት አይችልም ያሉት ኀላፊዋ ሌሎች ተቋማት ጋር በጋራ መሥራት ውጤታማ ሥራ ለመሥራት ያስችላል ነው ያሉት።
ቱሪዝሙን ለማነቃቃት ሁሉም ተቋማት የየራሳቸው ድርሻ እንዳላቸውም አንስተዋል። የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤቱ እያንዳንዱ ተቋማት ምን መሥራት እንዳላባቸው ድርሻቸውን የለየ ነው ብለዋል። የቱሪዝም መዳረሻዎች ሲለሙ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር፣ የአካባቢውን ባሕል፣ ታሪክ፣ ወግና እሴት ማስተዋወቅ እና ማኅበረሰብን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል ነው የተናገሩት።
ተንቀሳቃሽ እና የማይንቀሳቀሱ ቅርሶችን ጠብቆ ለማቆየት የጥገና እና የእድሳት ሥራ እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል። ቅርሶችን ለመጠበቅ የሚያስችል ሙዚየሞች እየተገነቡ መኾኑንም አመላክተዋል። ቋሚ ቅርሶችን ለመጠገን በጀት ተመድቦ እየተሠራ ነው ያሉት ኀላፊዋ በቅርስ ጥገና ሂደቱ ማኅበረሰቡ ተሳታፊ መኾኑንም ተናግረዋል።
የቅርስ ጥገና ሥራዎችን በፍጥነት ለመሥራት የጸጥታ ችግሩ እንቅፋት ኾኖ እንደቆየም አስታውሰዋል። የሰሜን ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኀላፊ በለጠ ጥጋቡ በዞኑ የሚገኙ የቱሪዝም ጸጋዎችን የሚጠብቅ፣ የሚንከባከብ እና ለትውልድ የሚያሸጋግር ተቋም በማስፈለጉ የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት መቋቋሙን ገልጸዋል። ሁሉም መምሪያዎች የምክር ቤቱ አባል መኾናቸውንም ተናግረዋል።
የቱሪዝም ሥራ በቅንጅት እና በመንሰላሰል እንደሚሠራም ገልጸዋል። እያንዳነዱ ተቋማት የራሳቸውን ድርሻ እና ኀላፊነት መወጣት እንደሚገባቸው አመላክተዋል። የቱሪዝም ዘርፉ አንዱ የምጣኔ ሃብት መሰሶ ነው ያሉት ምክትል አሥተዳዳሪው የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማት የቱሪዝም ገቢን ማሳደግ ይገባል ብለዋል። ዞኑም ለቱሪዝም ዘርፉ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ አስታውቀዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን