3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት ማጠናቀቁን የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።

13

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ የማስጀመሪያ መርሐ ግብር አካሂዷል።

‎የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ባለፈው ዓመት ከነበርንበት ችግር ወጥተን የተከልነው እያደገ፣ ሥራችን ፍሬ እያፈራ ከተማዋም በማንሠራራት ላይ ትገኛለች ብለዋል፡፡ ትውልዱ ታሪካዊ ኀላፊነቱን በመወጣት ሀገሩን ጠብቆ ወደፊት ለማሻገር ሊሠራ እንደሚገባም አሳስበዋል።

“በመትከል ማንሰራራት” የሚለውን ሀገራዊ መሪ መልዕክት በመያዝ የከተማዋን ውበት ከፍ የሚያደርግ ሥራ ሊሠራ እንደሚገባ ገልጸዋል። ከተማዋ በሐይቅ እና በወንዝ የተከበበች ከተማ ናት ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የበለጠ ውበቷን የሚመጨመር በደን የተከበበች አረንጓዴ ከተማ የመኾን ዕድል እንዳላት ተናግረዋል።

የባሕር ዳር ከተማ በተወሰነ ጥረት ውጤት ለማምጣት የሚቻልበት ተፈጥሮ እንዳላትም ገልጸዋል። ያለውን ዕድል በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም አሳስበዋል። ተፈጥሮን በትክክል በመጠቀም ባሕር ዳር ከተማን ጽዱ፣ በተክሎች ያሸበረቀች ከተማ ለማድረግ የነበረውን ችግኝ የመትከል እና የመንከባከብ ልምድ ማስቀጠል ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

የሚተተከሉ ችግኞችም ለተፈጥሮ ጥበቃ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው መኾን እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ የሰውዘር ደመላሽ የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ሚናው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ 16 ነጥብ 99 ሚሊዮን ችግኝ በከተማ አሥተዳደሩ መተከሉንም አንስተዋል፡፡ ዘንድሮ በተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት ተጠናቅቋል ነው ያሉት፡፡

ከዚህ ውስጥ 45 በመቶ የሚኾነው ለምግብነት የሚያገለግሉ የችግኝ አይነቶች መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡እነዚህን ችግኞች በኩታገጠም፣ በተፋሰስ እና በአርሶ አደር ጓሮ ለመትከል የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁንም ተናግረዋል፡፡

የመትከያ ቦታዎችን የመለየት፣ የጉድጓድ ዝግጅት እና ችግኝ የማጓጓዝ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል፡፡ እስካሁን 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ጉድጓዶች ተዘጋጅተዋል ነው ያሉት፡፡በችግኝ ተከላው ላይ አሚኮ ያገኛቸው የዘንዘልማ ቀበሌ ግብርና ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ አበባ ኀይሉ ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሥራ የችግኝ ዝግጅት እና የመትከያ ቦታ ዝግጅት ሥራዎችን ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።

የዘጌ 01 ቀበሌ ዋና አሥተዳዳሪ ሙሉጌታ ዳኘው ከዚህ በፊት ሥራዎችን አቅደው ሲሠሩ መቆየታቸውን ጠቁመዋል።በቀበሌው ችግኝ ተዘጋጅቶ እና የማጓጓዝ ሥራው ተጠናቅቆ ለተከላ ዝግጁ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ከማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ በኋላ በየቀበሌው ሕዝቡን በማነቃነቅ ተከላው እንደሚካሄድም ነው የተናገሩት፡፡

ዘጋቢ፡ ፍሬሕይወት አዘዘው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በወሩ እንደ ሀገር የሠለጠነ የፖለቲካ ባሕል እየጎለበተ እንዲመጣ ከባለድርሻ አባላት ጋር ውይይት አካሂደዋል።
Next articleቱሪዝሙን ለማነቃቃት ሁሉም ተቋማት የየራሳቸው ድርሻ ይወጡ።