አርሶ አደሮች እስከ ሐምሌ መጨረሻ ድረስ ሊዘሩ የሚችሉትን የሰብል ዓይነቶች መርጠው ቢዘሩ ውጤታማ ይኾናሉ።

11

ባሕር ዳር: ሰኔ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ዝናብ ዘግይቶ በገባባቸው አካባቢዎች አርሶ አደሮች እስከ ሐምሌ ወር መጨረሻ ድረስ ሊዘሩ የሚችሉትን የሰብል ዓይነቶች እንደየ ሥነ ምኅዳሩ ጠባይ ለይተው በመዝራት ምርት እና ማርታማነታቸውን ማረጋገጥ እንዲችሉ ግብርና ቢሮ አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በበኩሉ ከሰኔ 24 እስከ ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም በአብዛኛው የአማራ ክልል ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው የዝናብ ስርጭት ይኖረዋል ብሏል። አርሶ አደር ወርቁ ዳኜው በሰሜን ጎጃም ዞን የባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ የወንጀጣ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው።

እሳቸው እንደሚሉት አራት ቃዳ መሬታቸውን አርሰው በቆሎ ለመዝራት አስበው ነበር። ይኹንና ክረምቱ ዘግይቶ በመግባቱ እንዳሰቡት በቆሎ መዝራት አልቻሉም።እንደ አርሶ አደር ወርቁ ገለጻ ይህን እርሻ በጤፍ ሰብል ለመሸፈን ወስነዋል።

በሰሜን ጎጃም ዞን የቅንባባ ቀጣና የማቋል ንዑስ ቀበሌ ነዋሪ የኾኑት አርሶ አደር አያሌው ሞኝነት ዝናብ ዘግይቶ በመግባቱ እስካኹን መዝራት የነበረባቸውን ኑግ፣ ተልባ፣ ባቄላ እና አተር አለመዝራታቸውን ተናግረዋል።

“ፈጣሪን በመተማመን በደረቁ የዘራሁት በቆሎ ከሰሞኑ ዝናብ በመጣሉ መብቀል ጀምሯል። ቡቃያ በፍጥነት እንዲያድግም የአፈር ማዳበሪያ ሊቀርብልን ይገባል” ነው ያሉት። አርሶ አደሩ አያይዘውም ስንዴ፣ አተር፣ ባቄላ እና ኑግ ለመዝራት ባዘጋጁት ሰፊ ማሳ ላይም በምትኩ ጤፍ ለመዝራት ማቀዳቸውን ተናግረዋል።

የሰሜን ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኀላፊ በለጠ ጥጋቡ በዞኑ 315 ሺህ 539 ሄክታር መሬት በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች ለመሸፈን እየተሠራ ነው ብለዋል። 135 ሺህ ሄክታር መሬት በበቆሎ ለመሸፈን ታቅዶ እስካኹንም 86 ሺህ ሄክታር መሬት በበቆሎ ዘር መሸፈኑን ኀላፊው ተናግረዋል። ለዚህም 480 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች መሰራጨቱን ተናግረዋል።

በቀጣይ ለሚዘሩት የጤፍ፣ ዳጉሳ እና ለሌሎች ሰብሎች የሚኾን የአፈር ማዳበሪያ ደግሞ በመጓጓዝ ላይ ነው ። መኾኑም ግብዓት የዞኑ ችግር እንደማይኾን አቶ በለጠ አብራርተዋል።በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ከፍተኛ የሰብል ልማት ባለሙያ እንዬ አሰፋ በክልሉ ዝናብ ዘግይቶ በገባባቸው አካባቢዎች አርሶ አደሮች እስከ ሐምሌ ወር መጨረሻ ድረስ ሊዘሩ የሚችሉትን እንደየ ሥነ ምኅዳሩ ጠባይ በዋናነት ጤፍ፣ ስንዴ፣ ማሾ እና ቦሎቄ ሊዘሩ ይገባቸዋል ነው ያሉት።

በተለይ በምሥራቅ አማራ አካባቢ የሚገኙ አርሶ አደሮች ዝናብ ዘግይቶ በመግባቱ በረጅም ጊዜ የሚደርሰውን ማሽላ መዝራት እንዳልቻሉ አስታውሰዋል። ይኹንና በአጭር ጊዜ የሚደርሰውን የጊራና እንዲኹም ድቃይ የጊራናን ምርጥ ዘር እንዲጠቀሙ መክረዋል።

ምርጥ ዘር መሰራጨቱን የተናገሩት ባለሙያዋ አርሶ አደሮች የምርጥ ዘር እጥረት ቢገጥማቸው እንኳ ወቅቱ ሳያልፍ ያላቸውን ዘር አበጥረው ወይም ዘርን እርስ በእርስ ተለዋውጠው መዝራት እንዳለባቸው ነው የመከሩት። የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ከሰኔ 24 እስከ ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም ዝናብ ሰጭ የሚቲዎሮሎጂ ክስተቶች እየተጠናከሩ ይመጣሉ ብሏል።

ኢንስቲትዩቱ አክሎም በመጭው አንድ ወር ውስጥ በአማራ ክልል የሰሜን፣ ምዕራብ፣ መካከለኛው እና ደቡብ ጎንደር፣ የባሕር ዳር ዙሪያ፣ የአዊ፣ የሰሜን፣ ምዕራብ እና ምሥራቅ ጎጃም፣ ዋግ ኽምራ፣ የሰሜን እና ደቡብ ወሎ፣ የሰሜን ሸዋ ዞኖች፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ ነው ያለው።

በክልሉ በ2017/2018 የመኸር ወቅት 5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን 187 ሚሊዮን ኩንታል ለማምረት ታቅዶ እየተሠራ ነው። 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እንደሚቀርብም ከክልሉ ግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

ዘጋቢ:- ሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleታጣቂ ቡድኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየፈጸመባቸው መኾኑን የገነቴ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በወሩ እንደ ሀገር የሠለጠነ የፖለቲካ ባሕል እየጎለበተ እንዲመጣ ከባለድርሻ አባላት ጋር ውይይት አካሂደዋል።