አልማ በደቡብ ወሎ ዞን 250 የመማሪያ ክፍሎችን እያስገነባ ነው።

6

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት ከአባላት እና ከአጋር አካላት በተገኘ ሃብት የተለያዩ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። በተያዘው በጀት ዓመትም ማኅበሩ በትምህርት፣ ጤና እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መኾኑን የማኅበሩ መረጃ ያሳያል።

በበጀት ዓመቱ ከተሠሩ ሥራዎች ውስጥ ደግሞ በደቡብ ወሎ ዞን በተሁለደሬ ወረዳ የበደዶ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ ይገኝበታል። የበደዶ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህርት ነጃት ሙሐመድ ትምህርት ቤቱ ቀደም ብሎ በጭቃ እና በእንጨት የተሠራ ስለነበር በየጊዜው የመፍረስ አደጋ ሲያጋጥመው ቆይቷል።

ባለፉት ዓመታት በነበረው ጦርነትም በደረሰበት ጉዳት በመማር ማስተማሩ ላይ እንቅፋት ኾኖ መቆየቱን ነው ያስረዱት። በበጀት ዓመቱ በአልማ የተሠራው አራት ክፍሎች ያሉት ግንባታ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል ለሚገኙ ተማሪዎች በተሻለ ክፍል ውስጥ እንዲማሩ ማድረጉንም ገልጸዋል።

በትምህርት ቤቱ የሚገኙ የተጎሳቆሉ ክፍሎችን ደረጃ ለማሻሻል አጋዥ ድርጅቶች እና ማኅበረሰቡ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል። ትምህርት ቤቱ በ1980 የተመሠረተ ነው የተመሰረተው። አኹን ላይ 360 መደበኛ እና 118 ቅድመ መደበኛ ተማሪዎችን እያስተናገደ ይገኛል።

የደቡብ ወሎ ዞን አማራ ልማት ማኅበር (አልማ) ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር አበባው ታደሰ በ2017 በጀት ዓመት ለማሠባሠብ ከታቀደው 196 ሚሊዮን ብር እስከ አኹን በአይነት፣ በጉልበት እና በገንዘብ 142 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሃብት መሠብሠቡን ገልጸዋል።

250 የመማሪያ ክፍሎችም በተለያየ የግንባታ ሂደት ላይ ይገኛሉ። እስከ አኹን 24 ክፍሎች ተጠናቅቀዋል። እስከ ሐምሌ 15/2017 ዓ.ም ደግሞ ዘጠኝ ብሎኮችን ለማጠናቀቅ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። እስካኹን ለተጠናቀቁት እና በሂደት ላይ ለሚገኙት ግንባታዎች 64 ሚሊዮን ብር ወጭ ስለመደረጉም አስረድተዋል።

ዳይሬክተሩ በ2018 በጀት ዓመት ነባር ፕሮጀክቶች የሚጠናቀቁ ይኾናል፤ የአዳዲስ ፕሮጀክቶች ሥራም ይጀመራል ነው ያሉት። ከትምህርት ባለፈ ማኅበሩ በ26 ሚሊዮን 800 ሺህ ብር የተለያዩ የጤና ፕሮጀክቶች ግንባታ ማከናወኑንም ገልጸዋል።

የሥራ ዕድል ፈጠራ ሌላኛው ትኩረት የተሠጠው ጉዳይ መኾኑንም አብራርተዋል። በክልሉ የተፈጠረው የሰላም ኹኔታ ሥራዎችን ለመከታትል እንደ አንድ ችግር ተነስቷል። የማኅበሩ አባላት ለልማት የሚያዋጡትን ክፍያ በማሳደግ፣ አባል ያልኾኑ ደግሞ ማኅበሩን በመቀላቀል የክልሉን ልማት እንዲያግዙም ጠይቀዋል።

ዘጋቢ፦ዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleአዲስ የወጣው የአማራ ክልል የአሥተዳደር ሥነ ሥርዓት አዋጅ የመንግሥት ተቋማት አሠራር ግልጽ እና ተጠያቂ እንዲኾን የሚያስችል ነው።
Next articleታጣቂ ቡድኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየፈጸመባቸው መኾኑን የገነቴ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።