
ባሕር ዳር: ሰኔ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በክልሉ አዲስ በወጣው የአማራ ክልል አሥተዳደር ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 292/2017 ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በባሕር ዳር ከተማ እየተወያየ ነው።በውይይቱ ላይ የክልል እና የዞን ከፍተኛ መሪዎች፣ የከተማ ከንቲባዎች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው ይህ አዋጅ በመንግሥት ተቋማት ለሚወጡ መመሪያዎች እና ለሚሰጡ አሥተዳደራዊ ውሳኔዎች የሕግ ሥርዓት ለማበጀት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አብራርተዋል።
አዋጁ ተቋማት በሚያወጧቸው መመሪያዎች እና በሚያሳልፏቸው ውሳኔዎች ሕጋዊነት ላይ ቅሬታ ያለው አካል ለፍርድ ቤቶች ቅሬታውን የሚያሰማበትን ሥርዓት የሚዘረጋ የሕግ ማዕቀፍ ስለመኾኑም ጠቁመዋል።
የመንግሥት አሠራር ግልጽ እንዲኾን፤ ማንኛውም የመንግሥት ባለሥልጣን ለሚያጓድለው ኀላፊነት እንዲጠየቅ፣ የሕግ የበላይነት እና መልካም አሥተዳደርም እንዲሰፍን ያስችላል ነው ያሉት።
ይህ የሕግ ማዕቀፍ ለክልሉ እድገት አስተዋጽኦ ያለው መኾኑን በመረዳት በወጣበት አግባብ ተግባራዊ እንዲኾን ከፍተኛ አመራሩ እና ሕዝቡ በቂ ግንዛቤ ይዘውበት በጋራ መሠራት እንዳለበትም ፕሬዝዳንቱ መልዕክት አሥተላልፈዋል።
በመድረኩ ላይ የውይይት መነሻ ጥናት ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህር እና ተመራማሪ ሰለሞን ዓባይ (ዶ.ር) የአሥተዳደር ሥነ ሥርዓት ሕግ የመንግሥት ተቋማት በተሰጣቸው ሥልጣን መሠረት ለዜጎች አገልግሎት ሲሰጡ እና ውሳኔዎችን ሲወስኑ ሕግን ተከትለው እንዲኾን የሚያስችል ነው ብለዋል።
የሚያወጧቸው ተቋማዊ ሕግጋት እና ውሳኔዎች የሚፈተሹበት፣ ጉድለቶች ሲኖሩ የሚታረሙበት፣ ጥፋቶች ሲፈጸሙም የተቋማት መሪዎች ተጠያቂ የሚኾኑበት ነው ብለዋል። የሕግ ማዕቀፉ በአወጣጡ ልክ ተግባራዊ ሲደረግ ተቋማት በሚሠሯቸው ሥራዎች ሁሉ ግልጽ ይኾናሉ፤ ጥፋቶች ሲገኙም ተጠያቂ ይኾናሉ፤ መልካም አሥተዳደር ይሰፍናል፤ ዜጎችም የተጠቃሚነት መብታቸው ከፍ ይላል ብለዋል።
በመኾኑም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለዚህ የአሥተዳደር ሥነ ሥርዓት አዋጅ ተግባራዊነት የበኩላቸውን ማበርከት እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል። ይህ አዋጅ እንደሀገር በ2012 ዓ.ም ከወጣው የአሥተዳደር ሥነ ሥርዓት አዋጅ ተጣጥሞ የወጣ ስለመኾኑም ጠቁመዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን