
ደብረብርሃን፡ ሰኔ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ የ2017 ዓ.ም የአፈጻጸም ግምገማ እና የ2018 ዓ.ም የዕቅድ ትውውቅ በደብረ ብርሃን ከተማ እያካሄደ ነው፡፡ በመድረኩ የተገኙት የሰሜን ሽዋ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ ተክለየስ በለጠ በቅርብ ዓመታት በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት ትውልድ ላይ የደረሰው ተፅዕኖ የሚታወቀው ከዓመታት በኋላ ነው ብለዋል፡፡
የትምህርት ተግባራት ከየትኛውም ፍላጎት እና ጫና ነጻ ኾነው መከናወን የሚችሉበትን ዕድል መፍጠር ወቅቱ የሚጠይቀው ኀላፊነት መኾኑን ምክትል አሥተዳዳሪው ተናግረዋል፡፡ ለ2018 የትምህርት ዘመን ከወዲኹ በቂ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ የሚጠበቅ መኾኑን አቶ ተክለየስ ገልጸዋል፡፡
በትምህርት ዘርፉ ላይ ያጋጠመውን ተግዳሮት በመፍታት በቀጣዩ ዓመት የትምህርት ተቋማትን በሙሉ አቅም ሥራ ማስጀመር ቁልፍ ተልዕኮ ተደርጎ መወሰድ እንዳለበትም አቶ ተክለየስ አሳስበዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ አኹን ላይ ቀድሞ መሥራት ይጠይቃል ያሉት ምክትል አሥተዳዳሪው ችግሮችን ተጋፍጦ ማለፍ የሚጠይቅበት ጊዜ ነው ብለዋል።
ግጭት በበረታበት ወቅት የመማር ማስተማር ሂደት ፈታኝ ኾኖ መቆየቱን የገለጹት የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ፀጋዬ እንግዳወርቅ ከ400 በላይ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን ጠቅሰዋል። 238 ትምህርት ቤቶች በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ምክንያቶች ውድመት እንደደረሰባቸው መምሪያ ኀላፊው ገልጸዋል።
ለዚህም ችግሮችን መለየት እና ለቀጣይ የትምህርት ዘመን ማኅበረሰቡን ባለቤት የማድረግ ሥራ ከወዲኹ ለመሥራት ባለድርሻ አካላት ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡ በመድረኩ በምክትል ቢሮ ኀላፊ ደረጃ የሥራ እና ሥልጠና ቢሮ አማካሪ ድረሴ እሸቴ፣ የክልሉ ገጠር መንገድ ቢሮ ምክትል ላፊ አስራቴ አለኸኝን ጨምሮ የዞን የሥራ ኀላፊዎች፣ የወረዳ እና ከተማ አሥተዳደሮች፣ የትምህርት ዘርፍ የሥራ ኀላፊዎች እና ባለሙያዎች ተሳትፎ እያደረጉ ነው፡፡
ዘጋቢ፦ በላይ ተስፋዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን