የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳትፎ የመልካም ሰብዕና መገንቢያ መሣሪያ ነው።

41

አዲስ አበባ: ሰኔ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰዎች በራሳቸው ተነሳሽነት ያለቅድመ ሁኔታ የሚሠሩት በጎ ሥራ ነው፡፡ ለአገልግሎታቸውም ምላሽ እና ክፍያ አይጠይቁም። ሰዎች ሙያቸውን፣ ጊዜያቸውን፣ ሃብታቸውን ወይም ገንዘባቸውን ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሊያውሉ ይችላሉ።

“በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ መልዕክት” የ2017 ዓ.ም የወሰን ተሻጋሪ ወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ ግብር በአፋር ሰመራ ተጀምሯል። በመርሐ ግብሩ የአፋር ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ሐጅ አወል አርባ፣ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር)፣ የተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና ከመላው ኢትዮጵያ የተሰባሰቡ የወሰን ተሻጋሪ በጎ ተግባር ላይ የሚሳተፉ ወጣቶች ታድመዋል።

ወጣቶች ከሚኖሩበት አካባቢ ወጥተው በበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሳተፋቸው ማኅበራዊ ፋይዳን ያጎላል ያሉት ርእሰ መሥተዳድር አወል አርባ እህትማማችነት እና ወንደማማችነትን ያጠናክራል፤ ለዘላቂ ሰላምም የላቀ ሚና አለው ብለዋል።ወሰን ተሻግራችሁ ወደ አፋር የመጣችሁ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን እናመሰግናለን ያሉት ሐጂ አወል አርባ ለበጎ አገልግሎታቸው ውጥን ስኬትም የክልልሉ መንግሥት አስፈላገውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር) የወጣቶች የመልካም ሥራ ተሳትፎ የመልካም ሰብዕና መገንቢያ መሣሪያ ነው ብለዋል። ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሳተፋቸው አንድም ሰብዕናቸውን መገንቢያ ሌላም ሕዝባቸውን ማገልገያ እንደኾነ አንስተዋል።

በዚህ የክረምት ወራት የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሳተፍ ዕውቀታችሁን እና ጊዜያችሁን ተጠቅማችሁ ማኅበረሰባችሁን ለማገልገል ዝግጁ ስለኾናችሁ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያመሰግናል ነው ያሉት።አረንጓዴ አሻራ፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት መሥራት እና ማደስ፣ የአካባቢ ጽዳት፣ የትምህርት እና ሌሎች 14 ዘርፎች በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ይከወናሉ ብለዋል። የሰላም ግንባታው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አካል ተደርጎም ይከናወናል ብለዋል።

በወጣቶች የወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃድ አገልግሎት በርካታ ውጤቶች ተመዝግበዋል ያሉት ዶክተር ኤርጎጌ የተሻሻሉ የአሠራር ማዕቀፎችን በመንደፍ ለበለጠ ስኬት እየሠራ ነው ብለዋል።የዘንድሮው የክረምት ወራት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለአራተኛ ዙር የሚካሄድ ይኾናል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የደንበኞችን ብዛት 10 ሚሊዮን ማድረሱን አስታወቀ።
Next articleበቀጣይ ዓመት የትምህርት ተቋማትን በሙሉ አቅም ሥራ ማስጀመር ቁልፍ ተግባር ነው።