
አዲስ አበባ፡ ሰኔ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የቴሌኮም ፍቃድ አግኝቶ አገልግሎት መስጠት በጀመረበት አራት ዓመታት ውስጥ 10 ሚሊዮን የ90 ቀናት ንቁ ደንበኞች ማፍራቱን የድርጅቱ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ዊም ቫንሄለፑት ተናግረዋል።
ለስኬቱም አስተማማኝ እና ሁሉን አቀፍ የሞባይል ግንኙነት ፍላጎት መኖርን በምክንያትነት ጠቅሰዋል። ይህም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በተቋሙ ላይ ያላቸውን ዕምነት የሚያሳይ ነው ብለዋል። ጠንካራ የቴሌኮም እና የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶች መሠረተ ልማትን ለማስፋፋት ባለፉት አራት ዓመታት ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ ኢንቨስት ተደርጓል ነው ያሉት።
ሥራ አሥፈጻሚው በአሁኑ ጊዜ ፈጣን የአራተኛ ትውልድ ኔትወርክን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ ከግማሽ በላይ ለሚኾነው ተደራሽ ለማድረግ በከተሞች የኔትወርክ ማማዎች እየተዘረጉ ስለመኾናቸውም አስረድተዋል። የአገልግሎታቸው ተጠቃሚዎች ቁጥር በፍጥነት እያደገ በየቀኑ 31ሺህ አዳዲስ ደንበኞችን እያገኙ መኾናቸውን ዋና ሥራ አሥፈጻሚው ዊም ቫንሄለፑት አብራርተዋል።
ከተቋሙ 900 ሠራተኞች ውስጥ 97 በመቶ የሚኾኑት ኢትዮጵያውያን ናቸውም ብለዋል። ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አገልግሎቶቹን ተደራሽ ባደረገባቸው አካባቢዎች እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች በመድረስ ማኅበራዊ ኀላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ራሄል ደምሰው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን