
አዲስ አበባ፡ ሰኔ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የቀጣይ አቅጣጫ ላይ ትኩረት ያደረገ የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) ክልሉ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ኾኖም ቢኾን እንደ ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ በበጀት ዓመቱ የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን ገልጸዋል።
በከተሞች የፕላን ትግበራ አፈጻጸም፣ ከመሬት አጠቃቀም እና ሕገወጥ የመሬት ወረራን ከመከላከል አኳያ፣ በመሠረተ ልማት አፈጻጸም፣ በቤቶች ግንባታ ዘርፍ እና በከተሞች የኮሪደር ልማት የተሻለ አፈጻጸም ቢኖርም እነዚህን ተግባራት በላቀ ብቃት እና አቅም መተግበር እንደሚገባ ዶክተር አሕመዲን አንስተዋል።
በተለይም በክልሉ የከተሞች የኮሪደር ልማት ከዋና ዋና ከተሞች ባሻገር በትንንሽ ከተሞችም ጭምር በፍጥነት እየሰፋ መኾኑን የገለጹት ዶክተር አሕመዲን በቀጣይም ይሄንኑ ተሞክሮ በገጠር የኮሪደር ልማት ላይም መድገም እና ማኅበረሰቡን የልማቱ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
እንደመንግሥት ትኩረት በተደረገባቸው የአንድ ከተማ ፕሮጀክት፣ የኮደርስ ሥልጠና፣ የሌማት ትሩፋት እንዲኹም ከተረጂነት ወደ አምራችነት ለመሸጋገር በሚደረገው ጥረት በአማራ ክልል አበረታች ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል።በውይይት መድረኩ ላይ የአማራ ክልል ዞኖች እና የከተማ አሥተዳደር መሪዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፦ ቤተልሄም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን