የክልሉ ሕዝብ በአገልግሎት አሰጣጥ በተደጋጋሚ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ዘመናዊ አሠራርን መከተል ይገባል።

21

አዲስ አበባ፡ ሰኔ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በክልሉ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል እንቅስቃሴ ተጀምሯል። በአማራ ክልል አሁን ለተፈጠረው የሰላም ችግር ከዳረጉት ምክንያቶች መካከል አንዱ የአገልግሎት አሰጣጥ መኾኑ በተደጋጋሚ ሕዝቡ በሚያደርጋቸው ውይይቶች ይገልጻል።

ይህን ችግር መቅረፍ የሚያስችል እና በሕዝቡ እና በመንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል በሁለተኛው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የአገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል ትኩረት ተሰጥቶታል። በማሻሻያው መሠረትም በሀገር አቀፍ ደረጃ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ይፋ ተደርጎ ወደ ሥራ ተገብቷል።

ይህን ተሞክሮ መነሻ በማድረግም በአማራ ክልል በአራት ማዕከላት የመሶብ የአንድ ማዕከል ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል።ማዕከሉ በክልል ደረጃ በባሕር ዳር፣ ደሴ እና ጎንደር ከተሞች በቀዳሚነት ተግባራዊ ይደረግበታል።

የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ በልማት እና ሌሎች ተግባራት የሕዝብ እርካታ መፈጠሩን አስገንዝበዋል።ነገር ግን በአገልግሎት አሰጣጥ ሕዝቡ የተማረረባቸው ችግሮች አሉ ነው ያሉት።

በከተማው የሚተገበረው የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ የሕዝቡ የአገልግሎት አሰጣጥ ቅሬታ የሚፈታ በመኾኑ በ2018 ዓ.ሞ ወደ ሥራ ለማስገባት ተቋማትን በመለየት በቅንጅት እና በትብብር እየተሠራ ነው ብለዋል።

የክልሉ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ባንችዓምላክ ገብረማርያም በክልሉ የመሶብ አንድ ማዕከልን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል ሥራ ተጀምሯል። በክልሉ ምክትል ርእሰ መሥተዳደር መሪነት የክልሉ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የሚያስተባብረው የተለያዩ ተቋማት የተካተቱበት ኮሚቴ ተዋቅሯል።

ሕዝቡ በአገልግሎት አሰጣጣቸው የተማረረባቸው 10 ተቋማት ተለይተዋል። ማዕከሉ ተግባራዊ የሚኾንበትን ቦታ የመለየት የሕግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት በኩል ብዙ ርቀት መጓዝም ተችሏል። አገልግሎቱ ተግባራዊ የሚኾንበትን ሕንጻ መልሶ ማልማት የሚያስችል የዲዛይን ሥራ እየተሠራም ነው።

ከተቋማትም ጋር በተደረሰው መግባባት መሠረትም ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማስገባት የሚያስችል በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ የልምድ ልውውጥ ስለመካሄዱም ተናግረዋል። የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ የክልሉ ሕዝብ በአገልግሎት አሰጣጥ በተደጋጋሚ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በቴክኖሎጅ የዘመኑ አሠራሮችን መከተል እንደሚገባ አሳስበዋል።

በክልሉ ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ የተጀመረው የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ የሕዝቡን የዘመናት ጥያቄ የሚፈታ ነው። ለተግባራዊነቱም ምክር ቤቱ ከክትትል እና ቁጥጥር ባሻገር ተገቢውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ኢብራሂም ሙሃመድ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየሴት አደረጃጀቶች ሰላም እንዲሰፍን እና ልማት እንዲመጣ የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ በትኩረት እየተሠራ ነው።
Next articleየተጠባባቂ ጥሪ ማስታወቂያ፦