የሴት አደረጃጀቶች ሰላም እንዲሰፍን እና ልማት እንዲመጣ የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ በትኩረት እየተሠራ ነው።

31

ደሴ: ሰኔ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ሴት የሰላም አምባሳደሮችን ማደራጀት ለዘላቂ ሰላም ግንባታ” በሚል መሪ መልዕክት የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ ጽሕፈት ቤት ከሰላም ሚኒሥቴር ጋር በመተባበር በየአደረጃጀቱ ከሚገኙ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሴቶች ጋር ውይይት አካሂዷል።

መድረኩን የከፈቱት የሰላም ሚኒሥቴር የሚኒሥትሩ አማካሪ አበበ ወርቁ ሴቶች በሰላም እጦት ዋናዎቹ ተጎጂዎች ቢኾኑም ሰላምን ለማምጣት እና ለመጠበቅ ልዩ የኾነ ጥበብ እና ተሰጥኦ አላቸው ብለዋል።

ይህን በመገንዘብ ሰላም ሚኒሥቴር በሁሉም አካባቢዎች ካሉ የሴት አደረጃጀቶች ጋር ሰላም እንዲሰፍን፣ አንድነታችን እንዲረጋገጥ እና ልማት እንዲመጣ የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

በአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ክንፍ ኀላፊ እሌኒ ዓባይ ክልሉ ያጋጠመውን የሰላም እጦት ለመቅረፍ ሴቶች የማኅበረሰቡ ወሳኝ አካል በመኾናቸው ጉልህ ሚና መጫዎታቸውን ጠቅሰዋል።

አኹን ላለንበት አንጻራዊ ሰላም መገኘት ሴቶች ለሰላም እና ለልማታቸው አስቻይ ኹኔታዎችን ለመፍጠር በርካታ ሥራዎችን መሥራት መቻላቸውን ተናግረዋል።

የመድረኩ ተሳታፊ የኾኑት ፋጦዬ ሲራጅ ከዚህ ቀደም በተሠራ ሥራ የአካባቢያችንን እና የአጎራባች አካባቢዎችንም ሰላም እንዲመጣ ጥረት አድርገናል ብለዋል።

ከጦርነት እና ከዘረኝነት የሚገኝ ትርፍ ባለመኖሩ ተው ብለን ከየቤታችን በተሳሳተ መንገድ የወጡ ወንድሞችን መመለስ እና ለሰላም እና እርቅ መሥራት አለብን ሲሉ ተናግረዋል።

ሌላዋ ተሳታፊ ወርቅነሽ ይማም ደግሞ በተፈጠረላቸው አደረጃጀት እና በምናገኛቸው ትምህርቶች የአካባቢያቸውን ልማት ለማረጋገጥ እየሠሩ መኾናቸውን አንስተዋል።
ሴቷ የሰላም አምባሳደርነቷን ሁሌም ቢኾን ማስቀጠል አለባት ነው ያሉት።

የሥልጠና እና የውይይት መድረኩ በምሥራቅ አማራ በተለያዩ አደረጃጀቶች ውስጥ ያሉ መሪዎች፣ የሰላም ኮሚቴ ኾነው የሠሩ ሴቶች፣ ነጋዴ ሴቶች፣ ሴት ባለሀብቶች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች እና ሌሎችም ተሳትፈውበታል።

ዘጋቢ:- መሐመድ በቀለ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበጎንደር ከተማ የተሠሩ የልማት ሥራዎች ለነዋሪዎች ምቾትን የሚፈጥሩ መኾናቸውን የሚዲያ ባለሙያዎች ተናገሩ።
Next articleየክልሉ ሕዝብ በአገልግሎት አሰጣጥ በተደጋጋሚ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ዘመናዊ አሠራርን መከተል ይገባል።