በጎንደር ከተማ የተሠሩ የልማት ሥራዎች ለነዋሪዎች ምቾትን የሚፈጥሩ መኾናቸውን የሚዲያ ባለሙያዎች ተናገሩ።

15

ጎንደር: ሰኔ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የተወጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎች በጎንደር ከተማ የተሠሩ እና እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።

የሚዲያ ባለሙያዎች በሀገሪቱ እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን መመልከታቸው በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ ሥራ ለማከናወን እንደሚያስችላቸው ገለጸዋል።

በጉብኝታቸውም በጎንደር ከተማ እና አካባቢው እየተሠሩ ያሉትን የመገጭ ግድብ፣ የኮሪደር ልማት እና የጎንደር አብያተ መንግሥታት እድሳትን ተመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ፕረስ ደርጅት ምክትል ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ወንድም ተክሉ እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎች ለነዋሪዎች ምቾትን የሚፈጥሩ እና የጎንደር ከተማን የቀደመ ታሪክ በማቆየት የራስን አሻራ ጎን ለጎን የሚያሳርፉ ናቸው ብለዋል።

የመገጭ ግድብ የጎንደር ከተማ ለረዥም ጊዜ ሲነሳ የቆየውን የንጽሕ መጠጥ ውኃ ችግር እንደሚቀርፍም አንስተዋል።

የቀድሞ የጎንደር ዩኒቨርስቲ ተማሪ የነበረው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የመንግሥት ኮሙንኬሽን ጉዳዩች ባለሙያ እድገቱ በዛብህ በጎንደር ከተማ የተሠሩ የልማት ሥራዎች ግርምትን እንዳጫሩበት ተናግሯል።

የሚዲያ ባለሙያ ዋናው ተግባር የሚሠሩ የልማት ሥራዎችን ማሳየት ችግሮች ሲኖሩ ደግሞ ነቅሶ በማውጣት የሕዝብ ዓይን እና ጀሮ መኾን ነው ብለዋል።

ጎንደር ከተማን ከዚህ በፊት እንደማታውቅ የነገረችን የድሬድዋ መገናኝ ብዙኃን ኤጀንሲ ጋዜጠኛ ዘይነባ አህመድ የተመለከተቻቸው የልማት ሥራዎች ለነዋሪዎች ምቾትን የሚፈጥሩ መኾናቸውን ተናግራለች።

ወደ መጣችበት አካባቢ ስትመለስ በጎንደር እና አካባቢው እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎች ለሌሎች ለማስገንዘብ እንደሚረዳት ተናግራለች።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር ዲኤታ ከበደ ደሲሳ ጎንደርን ጨምሮ በሀገሪቱ ስድስት የተለያዩ አካባቢዎች የሚዲያ እና መንግሥት ባለሙያዎች ጉብኝት እያደረጉ ነው ብለዋል።

ጉብኝቱ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የልማት ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን ለማሳየት እንደሚረዳም ገልጸዋል።

ዘጋቢ:- ዳንኤል ወርቄ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article90 ሚሊየን ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ የ10 ዓመታት ብሔራዊ የንፁሕ ማብሰያ ፍኖተ ካርታ ይፋ ኾነ።
Next articleየሴት አደረጃጀቶች ሰላም እንዲሰፍን እና ልማት እንዲመጣ የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ በትኩረት እየተሠራ ነው።