90 ሚሊየን ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ የ10 ዓመታት ብሔራዊ የንፁሕ ማብሰያ ፍኖተ ካርታ ይፋ ኾነ።

16

አዲስ አበባ: ሰኔ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 90 ሚሊየን ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ የ10 ዓመታት ብሔራዊ ንፁሕ ማብሰያ ፍኖተ ካርታ ይፋ ኾኗል።

የውኃ እና ኢንጂነር ሚኒስትር ድኤታ ኢንጅነር ሱልጣን ዋሊ (ዶ.ር) ፍኖተ ካርታው 3 ነጥብ 38 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚሸፍን እና የሕዝብን ኑሮ የሚያሻሽል መኾኑን ገልጸዋል።

ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የሚኖርባት ኢትዮጵያ
ከ100 ሚሊዮን በላዩ ባሕላዊ ባዮማስ ነዳጆች እንደ ማገዶ፣ ከሰል እና ኩበት ላይ ጥገኛ በመኾን ለማብሰያነት ይጠቀማል።

ይህ ባሕላዊ የኃይል አማራጭ በሚያስከትለው የሕዝብ ጤና ቀውስ በየዓመቱ ከ63 ሺህ በላይ ሰዎችን ለሞት ይዳርጋል።

የባዮማስ ማገዶዎች በስፋት መጠቀማቸው የደን መጨፍጨፍን ያፋጥናል፣ የበካይ ጋዝ ልቀትን ይጨምራል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶች እና ልጃገረዶችን ውድ ጊዜ ያባክናል።

ይህንን ችግር ይቀርፋል የተባለ የ10 ዓመታት የንፁሕ ማብሰያ ፍኖተ ካርታ በውኃና እና ኢነርጅ ሚኒስቴር ይፋ ተደርጓል።

ለ10 ዓመታት እንደሚተገበር ይፋ የተደረገው የንፁህ ማብሰያ ፍኖተ ካርታ የዜጎችን ሕይዎት ያሻሽላል ነው ያሉት ሚኒስትር ድኤታው።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ፍኖተ ካርታውን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችሉ የፖሊሲ እና ስትራቴጅ ማነቆዎችን የሚፈቱ እርምጃዎችን መውሰዱን ገልጸዋል።

በንፁህ ማብሰያ አለመጠቀም ምክንያት ሀገሪቱ ከ30 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ምጣኔ ሃብታዊ ኪሳራ እንደሚያጋጥምም ተናግረዋል።

የግብርና ሚኒስትር ድኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤልያስ
ፍኖተ ካርታው የአፈር ለምነትን በማሻሻል ምርታማነትን እንደሚጨምር ገልጸዋል። ንጹሕ ምግብ ማብሰል የኃይል ጉዳይ ብቻ ሳይኾን የጤና እኩልነት እና የትምህርት እኩል ተሳታፊነት ጉዳይ ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጅ ቢሮ የባዮ ኢነርጂ ዳይሬክተር ወንድም በሪሁን ፍኖተ ካርታው በክልሉ የተጀመረውን እንቅስቃሴ ይበልጥ አጋዥ መኾኑን ገልጸዋል። ይፋ በተደረገው ፍኖተ ካርታ ሚኒስትሮች፣ የክልል ቢሮ የሥራ ኀላፊዎች እና አጋር አካላት ተገኝተዋል።

ዘጋቢ:- ኢብራሂም ሙሃመድ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleማዕከሉ በመረጃ ላይ የተመሠረተ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ለመሥጠት ያግዛል።
Next articleበጎንደር ከተማ የተሠሩ የልማት ሥራዎች ለነዋሪዎች ምቾትን የሚፈጥሩ መኾናቸውን የሚዲያ ባለሙያዎች ተናገሩ።