ማዕከሉ በመረጃ ላይ የተመሠረተ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ለመሥጠት ያግዛል።

8

ባሕር ዳር: ሰኔ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ማዕከሉ ባለፉት ሁለት ዓመታት ገደማ ባከናወናቸው ተግባራት ዙሪያ ከሚመለከታቸው ተቋማት እና አጋር አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።

የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ እንዳሉት ማዕከሉ መረጃን በሳይንሳዊ መንገድ ለመሰብሰብ፣ ለመተንተን እና ለመቀመር አቅም የሚኾን ነው። መረጃ የአንድን ሀገር እድገት የሚወስን በመኾኑ ለክልሉ ፕላን እና ልማት ቢሮ እንደ መረጃ ማዕከልነት ኾኖ ያገለግላል ነው ያሉት።

በየትኛውም ክፍለ ዓለማት የሚገኙ ተመራማሪዎች የክልሉን መረጃ ለምርምር ግብዓት እንዲጠቀሙበትም እድል ይፈጥራል ብለዋል። ማዕከሉ በመረጃ ላይ የተመሠረተ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ለመሥጠት እንደሚያግዝም ተናግረዋል።

የመረጃ ማዕከሉን ለማጠናከር ከተለያዩ ድርጅቶች እና በአማራ ክልል ከሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም
ጋር በጋር እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

በአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የክልላዊ ጤና እና ጤና ነክ መረጃ ቅመራ፣ ትንተና እና አሥተዳደር ማዕከል ዳይሬክተር እጸገነት ክንዴ ማዕከሉ ከተቋቋመ ጀምሮ ጤና እና ጤና ነክ የኾኑ ጥራት ያላቸው መረጃዎችን የመለየት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

የተለዩ መረጃዎችን ደግሞ ለሳይንሳዊ አገልግሎት እንዲውሉ በበይነ መረብ የመጫን ሥራ ተሠርቷል ብለዋል። አሁን ላይ መረጃዎችን በመተንተን ለውሳኔ ሰጭ አካላት የማቅረብ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። ማዕከሉ ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት እና ከተከሰተም በኋላ ተገቢውን ቁጥጥር ለማድረግ ትልቅ አቅም መኾኑን ነው የገለጹት።

በአማራ ክልል የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ዋና ጸሐፊ ታፈረ መላኩ (ዶ.ር) እንዳሉት የመረጃ ማዕከሉ የጤና ሥርዓቱን ለማሻሻል፣ በሽታዎችን ለመቆጣጠር፣ ፖሊሲ እና ስትራቴጂዎችን ለመቅረጽ ትልቅ አቅም ይኾናል።

በዩኒቨርሲቲዎች የሚሠሩ የምርምር ሥራዎችን በአንድ ማዕከል ለማደራጀት እንደሚያግዝም ገልጸዋል። ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ለምርምር መነሻነት ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል። የመረጃ ድግግሞሽን በማስቀረት በተመጠነ መንገድ ለመጠቀምም ያግዛል ነው ያሉት።

ዘጋቢ:- ዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleሳይንሳዊ እና ውጤታማ የችግኝ አተካከል ዘዴ የትኛው ነው?
Next article90 ሚሊየን ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ የ10 ዓመታት ብሔራዊ የንፁሕ ማብሰያ ፍኖተ ካርታ ይፋ ኾነ።