
ባሕር ዳር: ሰኔ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የክረምት ወቅት ለችግኝ ተከላ የተመቸ ነው። የችግኝ ተከላ ሥራ በኢትዮጵያ የተለመደ ነው። ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የተለየ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ይገኛል።
በመላ ሀገሪቱ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች በዘመቻ በማሳተፍ በየዓመቱ ችግኞች ይተከላሉ። ለመኾኑ ችግኞችን በዘመቻ ከመትከል ባለፈ ስንቶቻችን ስለሳይንሳዊ እና ውጤታማ የኾነ የችግኝ አተካከል ዘዴ ግንዛቤው ያለን?
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ደረጄ ማንደፍሮ ስለችግኝ ተከላ ሲነሳ የሚተከሉ ችግኞችን ከማዘጋጀት የሚጀምር ነው ይላሉ። ችግኞች የሚተከሉበትን ቦታ እና የአየር ንብረቱን ታሳቢ ያደረገ ሊኾን ይገባል ነው የሚሉት።
ለተከላ የተዘጋጁ ችግኞች ወደ መትከያ ቦታ ሲጓጓዙ አያያዛቸው በአግባቡ እና ጉዳት በማይደርስባቸው መልኩ መኾን እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡
ችግኞች ከመትከያ ጊዜያቸው ቀደም ብሎ የመትከያ ጉድጓድ መዘጋጀት አለበት፡፡ ይህም ለችግኙ በቂ እርጥበት እንዲኖረው እና አፈሩ እንዲለሰልስ ያደርገዋል ነው ያሉት፡፡ በቁፋሮ ጊዜ ከጉድጓዱ የሚወጣው ለም አፈር ሳይበተን በጥንቃቄ ወደ ጎን ኾኖ መቀመጥ እንዳለበትም አንስተዋል።
ጉድጓዶች ሲቆፈሩ እንደየ ችግኞች ቢለያይም በአማካይ ከአንድ ሜትር እስከ ሁለት ሜትር ርቀት ሊኖራቸው ይገባል። ይህ ብዙ ጊዜ ለባሕር ዛፍ፣ ግራቪሊያ፣ አካሽያ እና የተራቆተ አካባቢ ላይ የደን ሽፋን እንዲኖር ለማድረግ በሚተከሉ ችግኞች ላይ ይተገበራል ብለዋል፡፡
እንደ ማንጎ ያሉት ተክሎች ደግሞ በስድስት ሜትር፣ ፓፓያ እና ሙዝ በሦስት ሜትር ርቀት እና ብርቱካን በአራት ሜትር ርቀት እንዲኾኑ ይመከራል ነው ያሉት።
ጉድጓዶች ከተዘጋጁ በኋላ ችግኙ ከመተከሉ በፊት ጉድጓዱ ውስጥ ውኃ ካለ ውኃው መውጣት አለበት። ይህም በቂ የአየር ዝውውር እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል። ከዚያም ከተቆፈረው ለም አፈር አንድ አራተኛ የሚኾነውን ወደ ጉድጓዱ መመለስ አስፈላጊ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
ለተከላ የተዘጋጀው ችግኝ ጤነኛ መኾኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ያሉት ምክትል ኀላፊው ማረጋገጫውም ችግኙ ግንዱ ጠንካራ እና ቅጠሎቹ አረንጓዴ፣ የችግኙ ቁመት በአማካኝ ከ30 እስከ 45 ሳንቲ ሜትር ቁመት ያለው መኾን አለበት ነው ያሉት፡፡ የስሮቹ ቁመት ከ25 ሳንቲ ሜትር በላይ ከኾነ ማሳጠር አስፈላጊ ነው፡፡ ስሩ ረጅም ከኾነ ሲተከል ይታጠፍና እንዳይጸድቅ ያደርገዋል ብለዋል።
ችግኙ የተዘጋጀበትን ፕላስቲክ በጥንቃቄ በምላጭ ከላይ ወደ ታች በአንድ ጊዜ መሰንጠቅ አለበት፡፡ ይህም ችግኙ የያዘው አፈር እንዳይለቅ ወይም እንዳይረግፍ እንደሚያደርግ ነው የተናገሩት።
ፕላስቲኩን ከአንድ ጊዜ በላይ በምላጭ መሰንጠቅ እና በእጅ ማስወገድ የማይመከር እና የችግኙን አፈር እንዲረግፍ የሚያደርግ መኾኑን ገልጸዋል።
ችግኙን በሁለት እጅ አስተካክሎ በመያዝ እና ስሮቹ እንዳይታጠፉ በጥንቃቄ ወደ ጉድጓዱ በማስገባት፤ ጉድጓዱ እስኪሞላ አፈር መመለስ፣ አፈሩ በነፋስ እና በዝናብ እንዳይጠረግ በእጅ በተወሰነ መልኩ ማጥበቅ አስፈላጊ መኾኑን ገልጸዋል። ግንዱ ወደ መሬት መቀበር እንደሌለበትም ጠቁመዋል፡፡
ፕላስቲኮቹን ሰብስቦ በአግባቡ በማስወገድ አካባቢን ከብክለት መታደግ አስፈላጊ መኾኑን አመላክተዋል፡፡
ስለዚህ ሁላችንንም ትክክለኛውን የችግኝ አተካከል ዘዴ ተግባራዊ በማድረግ ችግኞችን መትከል ይገባናል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፡ ፍሬሕይዎት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን