
ወልድያ: ሰኔ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) እና ሌሎች የሥራ ኀላፊዎች የሰሜን ወሎ ዞን የቢሮ ሕንፃ ግንባታ አፈጻጸምን ጎብኝተዋል።የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር በዘመን ኮንስትራክሽን እየተገነባ ያለው የዞኑ አሥተዳደር ሕንጻ በ2008 ዓ.ም መጀመሩን አስታውሰዋል።
2013 ዓ.ም ከፊል ርክክብ ተደረጎ እንደነበርም ገልጸዋል። በሰሜኑ ጦርነት በደረሰበት ከፍተኛ ጉዳት አገልግሎት መስጠት ባለመቻሉ ያልተጠናቀቁ እና የተጎዱ የሕንፃው ክፍሎች ግንባታ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።የቢሮ ግንባታው አገልግሎት አሰጣጡን ከማዘመን ባለፈ ለቢሮ ኪራይ በዓመት እስከ 5 ሚሊየን ብር ይወጣ የነበረን ወጭ ይቀንሳል ነው ያሉት።
ግምባታው በ2018 በጀት ዓመት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ለማጠናቀቅ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) “ግንባታው ምቹ የሥራ ከባቢ በመፍጠር ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ነው” ብለዋል።
የቢሮው መጠናቀቅ በአገልጋይ እና በተገልጋይ ወገን የመልካም አሥተዳደር ችግርን ይቀርፋል ነው ያሉት። በተለይም በሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ለሚደራጀው ዲጂታል አገልግሎት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል። የቢሮው ግንባታ በርእሰ መሥተዳድሩ የቅርብ ክትትል ይደርገለታል ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ አስፈላጊውን በጀት በመመደብ ተገቢውን ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን