
ባሕር ዳር: ሰኔ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የግብርና ጥራትና ደኅንነት ባለሥልጣን በምርጥ ዘር ብዜት ከተሠማሩ ድርጅቶች ጋር ውይይት እያደረገ ነው። በውይይቱ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) የምርጥ ዘር አቅርቦት ለግብርና ሽግግር ወሳኝ ነው ብለዋል።
የዘር ጥራትን በመከታተል እና ጥራት ያለው ዘር ለአርሶ አደሮች እንዲደርስ በማድረግ በኩል እንደ ክልል ጥሩ ልምዶች ተገኝተዋል ብለዋል።በዘር አምራች ድርጅቶች በኩል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታየው ጥራት የሌለው ዘር የመቅረብ ችግር በትኩረት የሚታይ ጉዳይ እንደኾነም አንስተዋል።
በዘር አምራቾች የሚታዩ አጠቃላይ ኹኔታዎችን በመገምገም እንደ ክልል ጥራት ያለው ዘር ለማቅረብ የሚያስችል ተግባራት እየተከናወኑ መኾኑን አብራርተዋል። የዘር ጥራት ችግሮች በአመራረት ወቅት እና በአያያዝ ወቅት ሊያጋጥም እንደሚችል ጠቁመዋል። ትክክለኛ ችግሩን ለመለየት የሚያስችል ጥናት መደረጉንም ገልጸዋል።
በአማራ ክልል የግብርና ጥራትና ደኅንነት ባለሥልጣን አማካኝነት በመስክ ምልከታ በማድረግ በአመራረት እና በማከማቻ ወቅት ያለውን የዘር አያያዝ እና ጥራት ዙሪያ ጥናት አድርጓል ብለዋል።
በጥናቱም ዘር አቅራቢ ድርጅቶች በዝቅተኛ፣ በመካከለኛ እና በከፍተኛ ደረጃ መለየታቸውን አብራርተዋል። በዚኽም መሰረት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቶች እየተደረጉ መኾኑን ተናግረዋል።
በጥናቱ መሰረት ከደረጃ በታች በኾኑ አምራች ድርጅቶች ላይ የማያዳግም እርምጃ ይወሰዳል ነው ያሉት። በአንጻሩ በጥንካሬ የተለዩት አምራቾችን በማበረታታት ልምዱን የማስፋት ሥራ እንደሚሠራ አመላክተዋል።
የአማራ ክልል የግብርና ጥራትና ደኅንነት ባለሥልጣን ኀላፊ ፈንታሁን ስጦታው የዘር አምራቾች እውቀትን እና ቴክኖሎጂን በመጠቀም አርሶ አደሮችን ለስኬት የሚያበቃ ዘር በማምረት የክልሉ የጀርባ አጥንት ናቸው ብለዋል።
የምክክር መድረኩ ልምድ ያላቸው አምራቾች ለሌሎች ለማካፈል እና ተሞክሮ ለመለዋወጥ የሚያስችል መኾኑን ጠቁመዋል። አምራቾች እርስ በእርስ በመደጋገፍ ለክልሉ ግብርና እድገት የበኩላቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን