
እንጅባራ: ሰኔ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የብሔረሰቡ አሥተዳደሩ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ በ2017 ዓ.ም የክረምት ወራት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት እቅድ ዙሪያ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በእንጅባራ ከተማ ምክክር አካሂዷል።
“በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ መልዕክት በሚካሄደው የዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 14 የሥራ ዘርፎችም ተለይተዋል። የአረንጓዴ አሻራ፣ የደም ልገሳ፣ የከተሞች ፅዳት፣ የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት፣ የመንገድ ጥገና፣ የትምህርት ቁሳቁሶችን ማሰባሰብ፣ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት እና ሌሎችም በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የሚሳተፉባቸው የሥራ ዘርፎች ናቸው ተብሏል።
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ቃለአብ ከሃሊ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልጎሎት የእርስ በእርስ መረዳዳት ባሕል እንዲጎለብት እና ወጣቶች ማኅበራዊ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ እድል የፈጠረ መኾኑን ተናግረዋል።በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ500 ሺህ በላይ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ይሳተፋሉም ነው ያሉት።
ወጣቶች ገንዘባቸውን፣ ጉልበታቸውን እና እውቀታቸውን አቀናጅተው ይህን ማኅበራዊ ኀላፊነታቸውን በላቀ መልኩ እንዲወጡ በቂ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዓለሙ ሰውነት የመንግሥት የልማት ግቦችን ለማሳካት የወጣቶችን አቅም በአግባቡ መጠቀም ወሳኝ መኾኑን ተናግረዋል።
ወጣቶች ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሳተፍ በመንግሥት ያልተዳረሱ ልማቶችን በማልማት ያሳዩት ተነሳሽነት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባልም ብለዋል።mየሰላም እሴት ግንባታ ሥራዎች በዘንድሮ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ትኩረት የሚሰጡ እንደኾነም ኀላፊው ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን