
👉 “ለግንባታ ሥራው መጓተት ምክንያቱ በተቋራጩ በኩል የሚቀርብ የፀጥታ እና የግብዓት አቅርቦት ችግር ነው” ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ
👉 “ለግንባታው የተያዘው የቅድመ ክፍያ ገንዘብ በወቅቱ ባለመከፈሉ ምክንያት የሙዚዬሙን ግንባታ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማከናወን እንቅፋት ኾኖብናል” ዘመን ኮንስትራክሽን
👉 “ዘመን ኮንስትራክሽን ለገንዘብ ቢሮ እስከ አሁን የደረሰበትን የአፈጻጸም ክፍያ ማረጋገጫ ሰርትፍኬት ማቅረብ አልቻለም” የቱሪዝም እና የሰው ሃብት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
ባሕር ዳር: ሰኔ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሙዚዬም የሰው ልጅ ታሪክን፣ ዕውቀትን፣ ጥበብን፣ እሴትን እና ባሕልን አደራጅቶ ከትውልድ ትውልድ የሚያሻግር ተቋም ነው። ቀደምት የሰው ልጆች አሻራ የኾኑት ቅርሶች ሁሉ በአግባቡ ተመዝግበው እና ተሰንደው የሚገኙበት፣ ትናንትን ወደ ኋላ የምናይበት እና ለነገ የምንማርበት የዕውቀት ቤትም ነው።
ሙዚዬም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው። ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ተጠብቀው ይቀመጡበታል፤ የጎብኝዎች መዳረሻ ይኾናል፤ ገጽታን ይገነባል፤ ምጣኔ ሃብት ያመነጫል፤ ለጥናት እና ምርምር ማዕከል በመኾን ያገለግላል። ሊቀ ህሩያን በላይ መኮንን ደራሲ፣ የባሕል እና የታሪክ ተመራማሪ ናቸው። የአማራ ክልል ባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓት ማኀበርን እና የአማራ ክልል ደራስያን ማኀበርን በሊቀ መንበርነት እየመሩ ይገኛሉ።
ሊቀ ህሩያን በላይ መኮንን በአማራ ክልል የሚገኙ አያሌ ተንቀሳቃሽ ቅርሶችን፤ የአማራ ሕዝብ ወጉን፣ ባሕሉን፣ ትውፊቱን፣ እሴቱን ጠብቆ የሚያቆይ የተደራጀ ክልላዊ ሙዚዬም ባለመኖሩ ሲቆጩ መቆየታቸውን ነግረውናል። የተደራጀ ክልላዊ ሙዚዬም ባለመኖሩ ምክንያት እናቶቻችን እና አባቶቻችን ሲጠቀሙበት የነበሩ የቤት ዕቃዎች፣ ባሕላዊ መገልገያዎች፣ የእርሻ መሳሪያዎች፣ የጦር መሳሪያዎች እና ውድ ቅርሶች ጠፍተውብናል ብለዋል።
በተለያዩ መድረኮችም እንደ ሕዝብ የባሕል ማዕከል እና የሙዚዬም ግንባታ ጥያቄዎችን ሲያነሱ መቆየታቸውንም ተናግረዋል።አሁን ላይ የግንባታ ሥራው መጀመሩ እንዳስደሰታቸው ነግረውናል። የግንባታ ሂደቱ የተጓተተ በመኾኑ በፍጥነት ተጠናቅቆ ወደ ሥራ እንዲገባ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም አንስተዋል።እየዘገየ በሄደ ቁጥር ዳግም የማናገኛቸውን በርካታ ቅርሶች እያጣን መኾኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የቅርስ ጥበቃ እና እንክብካቤ ዳይሬክተር ጋሻዬ መለሠ በ2015 ዓ.ም ከክልሉ መንግሥት በተመደበ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ”የአማራ ሕዝብ ሙዚዬም” ግንባታ መጀመሩን ተናግረዋል። የሙዚዬሙ ግንባታም በ15 ሺህ 600 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ መኾኑንም አንስተዋል። የሙዚዬሙን የግንባታ ሂደት በባለቤትነት የሚከታተለው ቢሮው መኾኑን አስታውቀዋል።
ሙዚዬሙን በአራት ዓመታት በማጠናቀቅ ወደ ሥራ ለማስገባት የጊዜ ገደብ እንደተቀመጠለትም ገልጸዋል። አፈጻጸሙ ከተያዘለት የጊዜ ገደብ አንጻር ሲታይ ክፍተቶች የታዩበት መኾኑንም ተናግረዋል። ለግንባታ ሥራው መጓተት ምክንያቱ በሥራ ተቋራጭ ድርጅቱ በኩል የሚቀርቡ ከጸጥታ እና ከግብዓት አቅርቦት ችግሮች ጋር የተያያዙ ምክንያቶች እንደኾኑም አመላክተዋል።
እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ቢሮው ግንባታውን ከሚያከናውነው ከዘመን ኮንስትራክሽን መሪዎች ጋር በተደጋጋሚ መምከሩንም አንስተዋል። በዘመን ኮንስትራክሽን የአማራ ሕዝብ ሙዚዬም ግንባታ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አንድነት ቦጋለ ለግንባታው የተያዘው የቅድመ ክፍያ ገንዘብ በወቅቱ ባለመከፈሉ ምክንያት የሙዚዬሙን ግንባታ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማከናወን እንቅፋት ኾኖብናል ይላሉ።
እስከ አሁን ድረስ አሰሪ መሥሪያ ቤቱ በውሉ መሠረት ቅድመ ክፍያውን አለመፈፀሙ ለፕሮጀክቱ መጓተት ዋነኛ ምክንያት እንደኾነ ገልጸዋል። ክፍያው ከተከፈለ ድርጅቱ ሰፊ ሃብት እና የሰው ኃይል ተጠቅሞ በተያዘው የጊዜ ገደብ ግንባታውን ማጠናቀቅ እንደሚችል አመላክተዋል።
በአማራ ክልል ምክር ቤት የቱሪዝም እና የሰው ሃብት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አበራ ፈንታሁን ግንባታው እስከ አሁን 58 በመቶ መድረስ እንደነበረበት አንስተዋል። ነገር ግን አሁን ላይ የፊዚካል አፈጻጸሙ 12 በመቶ ብቻ መኾኑን ነው የተናገሩት። አፈጻጸሙን በተመለከተ ከሚመለከታቸው መሪዎች ጋር እየተገመገመ እና ክትትል እየተደረገበት መኾኑን አንስተዋል።
ዘመን ኮንስትራክሽን ለገንዘብ ቢሮ እስከ አሁን የደረሰበትን ተገቢውን የአፈጻጸም ክፍያ ማረጋገጫ ሰርትፍኬት ማቅረብ እንዳልቻለ በጋራ ገምግመናል ብለዋል። ቋሚ ኮሚቴው በክልሉ ገንዘብ ቢሮ እና በዘመን ኮንስትራክሽን በኩል የሚነሱትን ጉዳዮች መሠረት አድርጎ በማግባባት ወደ ተሻለ አፈጻጻም እንዲገባ በግብረ መልስ ማሳወቃቸውን አስታውቀዋል። በቀጣይም ችግሩን ለመፍታት በከፍተኛ መሪዎች ጭምር በትኩረት ተይዞ ክትትል እየተደረገበት መኾኑን አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበዉ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን