
ሁመራ: ሰኔ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ከወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ነዋሪዎች ጋር በሁመራ ከተማ ተወያይተዋል።
በውይይቱ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ፣ ሌሎች የሥራ ኀላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የወሰንና ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አባላትም ተገኝተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ በህውሓት አገዛዝ ዘመን በርካታ ግፍና በደል ተፈጽሞበታል ብለዋል። ለዚህ ደግሞ በማይካድራ ሕዝብ ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ የቅርብ ጊዜ ትውስታ መኾኑን አንስተዋል። ይሄ ግፍ የተፈጸመው አማራ ናችሁ ተብለን ያሉት ተሳታፊዎቹ ነፃነታችንን ከተጎናጸፍንበት ጊዜ ጀምሮ ሰላማችን ማረጋገጥ ችለናል ብለዋል።
ይሁን እንጂ የማንነት ጥያቄአችን እስካሁን ሕጋዊና ሀገራዊ እውቅና አለማግኘቱ ተገቢ አይደለም ነው ያሉት። ከዚህም ባለፈ በደም የተገኘውን ነፃነት በኀይል ለመንጠቅ የሚደረግን እንቅስቃሴ የማይቀበሉት መኾኑን ነው ተሳታፊዎቹ የተናገሩት። የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ለበርካታ ዘመናት ግፍና በደሎች ደርሰውበታል ብለዋል። ይሄንን በደልም የሰው ልጅ ሁሉ ይረዳዋል ነው ያሉት።
በዚህ ምክንያት የሚነሳውን የወሰንና የማንነት ጥያቄ ጉዳይ በብረትና በጉልበት ለመፍታት ማሰብ ተገቢ አለመኾኑን አንስተዋል። በየትኛውም ወገን በኩል ጉዳዩን ዘላቂ ሰላም በሚያመጣና ሕጋዊ ቅቡልነት ባለው መንገድ መፍታት እንደሚገባ አንስተዋል።
ጉዳዩን ከመሠረቱ መፈታት የሚቻለው ከጉልበት ይልቅ ሰላማዊ አማራጭን በመጠቀም መኾኑንም ገልጸዋል። የአማራ ክልል ሕዝብና መንግሥት በጉልበት የሚመጣበት ኀይል እስካልመጣ ድረስ ሰላማዊ አማራጭን እንደሚጠቀም አስገንዝበዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ተገቢ መኾኑን እናምናለን ብለዋል። ሰው ከመሬት በላይ ከፍ ብሎ መታየት አለበት ያሉት አቶ ጌታቸው የወልቃይትን ሕዝብ ሕዝቤ ነው ብሎ መቀበል እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የትግራይ ሕዝብ አጀንዳ የሰላም አጀንዳ መኾኑንም አንስተዋል። የህውሓት መሪዎች የትግራይ ሕዝብ ፍጹም የተለያዩ አካላት መኾናቸውንም ተናግረዋል። ሰላምን ለመፍጠርም ሁለቱን አካላት ለየብቻ መመልከት ጠቃሚ ነው ብለዋል። የማንነት ጥያቄ መኖሩን እናምናለን፣ ጥያቄው ግን በሕጋዊና በፍትሐዊ መንገድ መመለስ አለበት ነው ያሉት። ጥያቄው የግለሰብ ጥያቄ ባለመኾኑ የሕዝቡን ድምጽ መስማት ይገባልም ብለዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪና የወሰንና ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ በሰላማዊው የትግራይ ሕዝብ ላይ ችግር እንዲፈጠር አንፈልግም ነው ያሉት። የወልቃይት ጠገዴን ሕዝብ የዘመናት ጥያቄ በአግባቡ መፍታት እንደሚገባ አሳስበዋል። ጥያቄው ሕጋዊና ሀገራዊ መልስ ያሻዋል ነው ያሉት።
የወሰንና ማንነት ኮሚቴው የሚያነሳው ይህ ጥያቄ የሕዝቡ ጥያቄ ነው ያሉት ኮሎኔል ደመቀ ጥያቄውን በአግባቡ አለመመለስ እንደገና በደልና ደም መፋሰስ እንዳያስከትል በጥንቃቄ ሊታይ እንደሚገባ ጠቁመዋል። የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው የህውሓት እንቅስቃሴ ከሰላማዊ መንገድ ያፈነገጠ በመኾኑ ለሁለቱ ሕዝቦች ሰላም ጠንቅ ነው ብለዋል።
የህውሓት አካሄድ ማንንም አይጠቅምም ያሉት አቶ አሸተ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ የማንነትና ወሰን ጥያቄን በሰላማዊ መንገድ ለመፍትታ ጥረት እያደረጉ መኾናቸውን ገልጸዋል። ከሰላም እንጂ ከጦርነት አትራፊ የሚኾን ባለመኖሩ ለሀገርና ለሕዝብ የሚበጀውን ሰላማዊ አማራጭ መከተል ተገቢ ነው ብለን እናምናለን ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን