
ሰቆጣ: ሰኔ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 35ኛው የአፍሪካ ሕጻናት ቀን “የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድን ለማነጽ ሕጻናት ተኮር ተግባራትን እንከውን” በሚል መሪ መልዕክት በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰቆጣ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ዋና አሥተዳዳሪ ኃይሉ ግርማይ ሀገራችን ኢትዮጵያ የሕጻናትን መብት ለማስከበር ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በመፈረም በርካታ ሥራዎችን እየሠራች መኾኗን አውስተዋል። የነገን ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለመፍጠር ዛሬ ላይ ሕጻናትን ማነጽ እንደሚገባ ነው አቶ ኃይሉ የገለጹት።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩም የሕጻናት ፓርላማ በማቋቋም በትኩረት እየተሠራ እንደኾነ የጠቆሙት ዋና አሥተዳዳሪው የሕጻናት ማቆያ ከመገንባት ጀምሮ ሌሎች አሥፈላጊውን ተግባር እንደሚከውኑ ጠቅሰዋል። በሕጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በመከላከል እና ከትምህርት ገበታ የራቁ ሕጻናትን ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ በማድረግ በኩል በየወረዳው ካሉ የሕጻናት ፓርላማ አባላት ጋር በትብብር መሥራታቸውን የሕጻናት ፓርላማ ዋና አፈ ጉባኤ አኳ ዘሩ ገልጿል። በቀጣይም በአረንጓዴ አሻራ ሕጻናት እንዲሳተፉ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት እንቅስቃሴ ሥራ መሥራታቸውን የሕጻናት ፓርላማ አፈ ጉባኤው ጠቁሟል።
ብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ የሕጻናት መቆያ በመገንባት የመንግሥት ሴት ሠራተኞች ተረጋግተው ሕዝብ እና መንግሥትን እንዲያገለግሉ የሚረዳ ማቆያ ለአገልግሎት ክፍት መኾኑን የተናገሩት ደግሞ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳዮች መምሪያ ኀላፊ ትበርህ ታደሰ ናቸው።
በአፍሪካ ለ35ኛ ጊዜ የሚከበረው የሕጻናት ቀን ለልጆች ብቻ ሳይኾን ለእናቶችም በሚጠቅም መልኩ መከበሩን ነው ያብራሩት። የሕጻናት ማቆያ መገንባቱ እናቶች ያለጭንቀት ሥራቸውን እንዲሠሩ ከማድረጉም ባሻገር የሕጻናትን የአመጋገብ ሥርዓት የሚያስተካክል ተግባር መኾኑን የመንግሥት ሠራተኛ የኾኑት ወይዘሮ አጸደ አበራ እና ወይዘሮ አበጁ ወዳጅ ተናግረዋል። ይህ የሕጻናት ማቆያም በመዋቅር ደረጃ ወርዶ እስከ ወረዳ ድረስ ቢቀጥል ለመንግሥትም፣ ለእናቶችም ፋይዳው የጎላ መኾኑን ገልጸዋል።
የሕጻናት ማቆያውንም የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ዋና አሥተዳዳሪ ኃይሉ ግርማይ እና የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ምክትል አሥተዳዳሪ እና የኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ሹመት ጥላሁን መርቀው ከፍተውታል። በበዓሉም የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከፍተኛ መሪዎች፣ የየወረዳ ኀላፊዎች፣ የሕጻናት ፓርላማ አባላት፣ ሕጻናት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ:- ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን