
ባሕር ዳር: ሰኔ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ችግሮቻቸውን ለመፍታት፣ ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት፣ ሰላማዊ መንገድን ለማስፋት ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አቋቁመው እየሠሩ ነው። በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑም በንቃት እየተሳተፉ ነው።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ችግሮቻቸውን እንደሚፈታላቸው፣ በኢትዮጵያ ላይ ምክክርን ባሕል እንደሚያደርግላቸው፣ ሰላምን በዘላቂነት መሠረት እንደሚያስይዝላቸው ተስፋ አድርገውበታል። የእስካሁኑ ሂደትም ተስፋቸውን የበለጠ የሚያጎላ ነው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ.ር) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሦስት ዋና ዋና ዓላማዎችን ይዞ መነሳቱን ገልጸዋል። አንደኛው ሀገራዊ መግባባትን ማምጣት፣ ሁለተኛው በሕዝብ እና በመንግሥት፣ በሕዝብ እና በሕዝብ መካከል መተማመን እንዲፈጠር ማድረግ፣ ሦስተኛው እንደ ሀገር ምክክርን ባሕል እንዲኾን ማድረግ ናቸው ብለዋል።
ሦስት ዋና ዋና ግቦችን ለማሳካት በርካታ ሥራዎችን መሥራታቸውን ገልጸዋል። የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይኾን በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንንም እንደሚያሳትፍ ነው የተናገሩት። አካታችነት እና አሳታፊነት በሚሉ መርኾዎቹ አማካኝነት አጀንዳ አለኝ የሚሉ ሁሉ አጀንዳቸውን በፈለጉት አማራጭ ማቅረብ ይችላሉ።
በ21ኛው ክፍለ ዘመን ንግግራችን፣ ውይይታችን ዕውቀት እና ምርምር መር መኾን አለበት የሚሉት ኮሚሽነሩ ሀገራዊ ምክክር በሕዝብ ዘንድ ምን ያክል ተቀባይነት አለው የሚለውን ሳይንሳዊ ምርምር ተደርጓል ነው የሚሉት። የተደረጉ ጥናቶች ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ለሰላም ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው፣ ተዓማኒ እንደኾነ የሚያመላክቱ ናቸው ብለዋል። በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የተሳተፉ ወገኖችም የዘመናት ችግሮቻችንን እና ጥያቄዎቻችንን ሁሉ ሰምታችሁናል፣ በነጻነት አቅርበናል፣ እናመሰግናለን እያሉ ይመጣሉ ነው ያሉት።
ግጭቶችን ማስቆም እና መፍታት የሚቻለው በምክክር ብቻ ነው ብለዋል። “የምንግባባው፣ አንዳችን የሌላችን ቁስል የምናክመው መነጋገር እና መመካከር ስንችል ነው” ይላሉ ኮሚሽነሩ። የሃሳብ አካታችነት፣ ተዓማኒነት፣ ግልጸኝነት ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ወሳኝ ጉዳዮች መኾናቸውን ገልጸዋል። በትጥቅ ትግል ውስጥ ያሉ አንዳንድ ታጣቂዎችም አጀንዳዎቻቸውን ማቅረባቸውን ነው የተናገሩት። ሌሎችም እንደሚያመጡ ተስፋ አለን ነው ያሉት።
“ሰላምን በሰላማዊ መንገድ እንዴት ማምጣት እንደሚቻል በተግባር እያየን ነው” ያሉት ኮሚሽነሩ እስካሁን ድረስ የሄድንባቸው መንገዶች ጥሩዎች ናቸው፣ የሚሰጡን መልሶች አወንታዊ ናቸው፣ ጥረታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል። ጅምሩ ተስፋ ሰጪ መኾኑንም ተናግረዋል። ታጣቂዎችን በሌሎች ወገኖች አማካኝነት እያገኟቸው መኾናቸውን ነው የገለጹት።
ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ መኾናቸውንም ተናግረዋል። ኀላፊነት በመውሰድ ለሀገራቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው ብለዋል። ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ያነሱት ኮሚሽነሩ የምሁራን አስተዋጽኦ ላቅ ያለ መኾኑንም አንስተዋል።
የሚቀሩ አጀንዳዎችን የመሰብሰብ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል። የሰላም ሥራ መልካም ሥራ ስለኾነ ቀሪ ሥራዎቻችን ውጤታማ እንደሚኾኑ ተስፋ እናደርጋለን ነው ያሉት። ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግን የፖለቲካ አውድ ለመፍጠር ምክክርን ባሕል ማድረግ ወሳኝ መኾኑንም ተናግረዋል። ሁላችንም የምንመኘው ሰላም እንዲሰፍን ባለን አቅም ሁሉ እየሠራን ነው ብለዋል።
ፈተናዎችን እያለፍን በርካታ ሥራዎችን ሠርተናል፣ አሁንም ውጤታማ ሥራ እንደምንሠራ እናምናለን፣ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም እና ምክክርን ይፈልጋል ነው ያሉት። ሰላምን በሰላማዊ መንገድ የማምጣት ሂደት መልካም ነው፣ የስኬት መለኪያውም ሂደቱ ነው፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያደሩ ችግሮች መፍትሔ የሚኾነው ምክክር እና ምክክር ብቻ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያውያን አንድነት ጠንካራ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ የኢትዮጵያውያንን አንድነት እያወጡ ለሕዝብ ማስተዋወቅ፣ የምክክርን አስፈላጊነት የማጉላት ኀላፊነት ሚዲያዎች እንዳለባቸውም ገልጸዋል። መንግሥት፣ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና መላው ኢትዮጵያውያን አስተዋጽዖቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያውያን ለሰላም እሺ፣ ለጦርነት እና ለግጭት ደግሞ እምቢ ማለት አለባቸው ነው ያሉት። ይቻላል ብለን ከተነሳን ሰላም ይሰፍናል ብለዋል። በጫካ ለሚገኙ ወንድሞቻችን የምናቅርበው ጥሪ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥነው የእውነት መመካከር ነው፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ናቸው፣ ለምን የእነዚህን ወገኖቻችን ተስፋ እናጨልማለን፣ ለልጆቻችን ማሰብ አለብን፣ የልጆቻችን ተስፋ እንዲለመለም ለእውነተኛ ሰላም እና ለእርቅ እንድትዘጋጁ እንጠይቃችኋለን ነው የሚሉት። ወደ ጫካ የወሰዳችሁን አጀንዳ ስጡን፣ እንመካከር፣ በመመካከር ያልፍልናል፣ ችግሮቻችንን እንፈታለን ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን