
ደብረ ማርቆስ: ሰኔ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት ከተማ አሥተዳደሩ የዜጎችን የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት እየሠራ ነው።
በ2014 ዓ.ም እና በ2015 ዓ.ም በ498 ማኅበራት ለተደራጁ ከ9 ሺህ በላይ ዜጎች የቤት መስሪያ ቦታ ማስተላለፉን አስታውሰዋል፡፡ ኾኖም በ2015 ዓ.ም መጨረሻ ያጋጠመው የጸጥታ ችግር ለሥራው እንቅፋት ኾኖ መቆየቱን አንስተዋል፡፡
በ2016 ዓ.ም በ5 ማኅበራት ለተደራጁ 79 ግለሰቦች የቤት መስሪያ ቦታ መተላለፉን የገለጹት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ በልዩ ሁኔታ በ87 ማኅበራት ተደራጅተው ለሚጠባበቁ የጸጥታ አካላት ቦታ ለማስተላለፍ የማጣራት እና ሕጋዊ የማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን አመላክተዋል፡፡
ዜጎችን የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ ማድረግ የከተማ አሥተዳደሩ ቁልፍ ተግባር እንደኾነ የገለጹት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በሊዝ፣ በምደባ፣ በግል እና በመንግሥት ትብብር እንዲሁም በመንግሥት እና በባለሃብቶች ቅንጅት ቦታ የማስተላለፍ እና ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ የማድረግ ተግባራት እየተከናወኑ መኾናቸውን ጠቁመዋል፡፡
የጸጥታ ችግሩ ካስከተለው ውስንነት በተጨማሪ በከተማ የሚስተዋለውን ሕገ ወጥ የመሬት ወረራ ለመቆጣጠር እና መልክ ለማስያዝ በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም አብራርተዋል፡፡የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ጥያቄ ያላቸው ዜጎች የኢኮኖሚ አቅማቸውን ባማከለ መልኩ ወደ ግንባታ የሚገቡበትን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት እንዲሁም ውስን የኾነውን የከተማዋን የመሬት ሃብት በአግባቡ ለመጠቀም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው ተብሏል፡፡
በከተማ አሥተዳደሩ ስር ከሚገኙ 20 ቀበሌዎች ውስጥ 6ቱ የገጠር ቀበሌዎች በመኾናቸው እና አንዳንድ ቀበሌዎች ከጸጥታ ችግር ያልተላቀቁ በመኾናቸው በልበሙሉነት ማኅበራትን ለማደራጀት እና ቦታ ለማስተላለፍ እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡
የከተማውን ሰላም የተሟላ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በማኅበር ተደራጅተው እየቆጠቡ የሚገኙ የከተማው ነዋሪዎች ሕጋዊ መስመርን ተከትለው እስከመጡ ድረስ ከተማ አሥተዳደሩ በይፋ የቤት ማኅበራትን ማደራጀት ሲጀምር የሚስተናገዱ መኾኑን አውቀው በትዕግስት እንዲጠባበቁ አሳስበዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን