የትምህርት ቤቱን ሀገር አቀፍ ውጤታማነት ለማስቀጠል መዘጋጀታቸውን የይሁኔ ወልዱ መታሰቢያ ደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ተናገሩ።

30

ደሴ: ሰኔ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ተማሪ ዮሴፍ በላቸው ከምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ነው የመጣው። ከ9 እስከ 12ኛ ክፍል ላለፉት 4 ዓመታት በይሁኔ ወልዱ መታሰቢያ ደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ትምህርቱን ተከታትሏል። በዚህ ዓመት ደግሞ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈታኝ ነው።

ተማሪ ዮሴፍ በትምህርት ቤቱ የተሻለ ትምህርት ማግኘቱን እና ለፈተናውም በበቂ ሁኔታ እየተዘጋጀ መኾኑን ለአሚኮ ተናግሯል። መምህራን በሚገባ አዘጋጅተውናል፣ ማንኛውም ግልጽ ያልኾነልንን ነገር በየትኛውም ጊዜ ጠይቀን መልስ ይሰጡናል ያለው ተማሪው አሁን ላይ በትኩረት ጥናት ላይ መኾኑን ነው የገለጸው።

የይሁኔ ወልዱ መታሰቢያ ደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የኾኑት ከደቡብ ጎንደር አውራምባ የመጣችው ተማሪ ሰላም አዳቤ እና ከሰሜን ጎንደር ጃናሞራ የመጣው ተማሪ ወርቁ ሙሉሰው በበኩላቸው ከዚህ በፊት ትምህርት ቤቱ በሀገር አቀፍ ፈተናዎች ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች የነበሩ መኾኑን አስታውሰዋል። የትምህርት ቤቱን ሀገር አቀፍ ውጤታማነት ለማስቀጠል መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።

የይሁኔ ወልዱ መታሰቢያ ደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር በለጠ ኀይሌ ትምህርት ቤቱ በ2017 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና 52 ተማሪዎችን እንደሚያስፈትኑ ገልጸዋል። የዘንድሮ ተፈታኝ ተማሪዎች ከፍተኛ አቅም ያላቸው መኾናቸውን የተናገሩት ርእሰ መምህሩ ከፍተኛ ውጤት ያመጣሉ ብለን እናምናለን ነው ያሉት።

ትምህርት ቤቱ ተማሪዎች በብሔራዊ ፈተና የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ እያገዘ ነው ብለዋል። አይቲ እና ቤተ መጽሐፍት በፈለጉት ሰዓት እንዲጠቀሙም መደረጉን አስረድተዋል።ትምህርት ቤቱ ባለፉት ሦስት ዓመታት ያስፈተናቸውን ተማሪዎች በሙሉ አሳልፏል። ከሁለት ዓመት በፊት ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛውን ውጤት ማስመዝገብ ችሏል።

ዘጋቢ:- ከድር አሊ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከሚዲያ ባለሞያዎች ጋር ተወያዩ።
Next articleየውጭ ሀገር ሥራ ሥምሪት ረቂቅ አዋጅ የዜጎችን መብት፣ ደኅንነት እና ዘላቂ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው።