በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በከተማ ግብርና ሥራ የተሰማሩ ሴቶች ውጤታማ መኾናቸውን ተናገሩ፡፡

17

ባሕር ዳር: ሰኔ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ወይዘሮ ገነት አበባው የገነት፣ ዮሴፍ እና ጓደኞቻቸው የዓሣ፣ ዶሮ ርባታና የተቀናጀ ግብርና ሽርክና ማኅበር መስራች እና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ በዓሣ፣ ዶሮ ርባታ፣ በአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ዘርፍ ተሰማርተው በባሕር ዳር ከተማ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሬስቶራንት እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡

በአትክልትና ፍራፍሬ ማምረት እና በ20 ዶሮዎች የዶሮ ርባታ ሥራ እንደጀመሩ የሚናገሩት ወይዘሮ ገነት አሁን ላይ የአትክልት እና ፍራፍሬ ማምረት፣ ሠፊ የዶሮ ርባታ እና በዘመናዊ መልኩ በተሠሩ ኩሬዎች የዓሣ ማምረት ሥራ እየሠሩ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡

የሚሠሩት ሥራ የተቀናጀ የከተማ ግብርና መኾኑ የዓሣዎች ጽዳጅ እና ውኃ ያለማዳበሪያ የአትክልትና ፍራፍሬ ለማምረት ይውላል፣ የዶሮዎች ጽዳጅ ደግሞ ለዓሳዎች መኖ እንደሚጠቀሙበት እና በተመሳሳይ የአትክልትና ፍራፍሬ ቀሪው ተረፈ ምርት ደግሞ ለዶሮዎች እና ለዓሣዎች መኖነት የሚውል መኾኑን ነው ወይዘሮ ገነት የተናገሩት፡፡

ለወደፊትም በማምረቻ ቦታው አቅራቢያ ሬስቶራንት በመክፈት ትኩስ ምርቶችን ለኅብረተሰቡ ለማቅረብ አቅደው እየሠሩ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ምርቶቻቸውን ለመላክ አስበው እየሠሩ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ሥራ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳድረው አሸናፊ ኾነውም ተሸልመዋል፡፡

በአራት ሠራተኞች የጀምሩት ሥራ አሁን ላይ ከቤተሰቦቻቸው በተጨማሪ ለ15 ዜጎች የሥራ ዕድል እንደፈጠሩ ገልጸዋል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ሀብት እንዳፈሩም ነው ያመላከቱት። ሌላኛዋ ተጠቃሚ ወይዘሮ ብዙሀረግ ታደሰ በከብት ርባታ እና በወተት ልማት ዘርፍ ተሰማርተው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ሥራ የጀመሩት በዶሮ ርባታ ሲኾን አሁን ላይ የከብት ርባታ ሥራ ላይ ተሰማርተው እየሠሩ ውጤታማ መኾናቸውን ተናግረዋል።

በዚህም ኑሮአቸውን የተሻለ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ የከብት ርባታው ከ2 ከብቶች ተጀምሮ አሁን 17 መድረሳቸውን ገልጸዋል። ወደ ገንዘብ ሲቀየር በሚሊዮን የሚቆጠር ሀብት ማፍራታቸውን ነው የተናገሩት፡፡ በቀጣይ የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ለመጀመር አቅደው እየተንቀሳቀሱ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሰብለ ዘውዱ በባሕር ዳር ከተማ በርካታ ሴቶች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሰማርተው ውጤታማ ኾነዋል ነው ያሉት። ከራሳቸው አልፈውን ለሌሎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ስኬታማ እንደኾኑ ገልጸዋል፡፡ ለሌሎች ሴቶች በአርዓርያነት የሚጠቀሱ እንደኾኑም ጠቁመዋል፡፡

ሥራዎቻቸውን ሊያጠናክር በሚችል መልኩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች፣ ሥልጠና፣ የመስሪያ ቦታ እና የብድር አቅርቦት እንዲያገኙ የማገዝ እና የማስተባበር ሥራዎችን እየሠሩ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የሴቶችን ምጣኔ ሀብት አቅም ማሳደግ ለሀገር ዕድገትም አስተዋፅኦው ከፍተኛ መኾኑን ነው የገለጹት፡፡

ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራዎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ይሠራል።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከሚዲያ ባለሞያዎች ጋር ተወያዩ።