
ባሕር ዳር: ሰኔ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) እንደዛሬው የትምህርት ተቋማት ባልበዙበት ከዛሬ 20 ዓመት በፊት ሦስተኛ እና ሁለተኛ ዲግሪ ቀርቶ የመጀመሪያ ዲግሪ መያዝም ብርቅ እና ድንቅ ነበር፡፡ ባለዲግሪዎቹም በእውቀታቸው ስለሚሠሩ ቅቡልነትም አላቸው፡፡
በዚያው ዘመን የነበረው መሪ አልተማረም በሚል አስተሳሰብ “ያልተማረ አይገዛንም” የሚል ፖለቲካዊ ሀሳብም ይቀነቀን ነበር፡፡በምርጫ 97 የፖለቲካ ትኩሳትም ተቃዋሚዎች ዶክተርነት እና ኢንጅነርነትን መታገያም መወዳደሪም መስፈርት እስከ ማድረግ ደርሰው ነበር፡፡
ቀደም ብሎ ቢጀመርም ከምርጫ 97 የፖለቲካ ትግል በኋላ የመንግሥትም የግልም የትምህርት ተቋማት በብዛት ተከፈቱ፡፡ በተጓዳኝም በየጊዜው የተደረጉ የመንግሥት ተቋማትን መልሶ የማደራጀት ሥራዎች የትምህርት ዝግጅትን መስፈርት ያደረጉ ነበሩ።
ፖለቲካው፣ የሲቪል ሰርቪስ አደረጃጀቱ፣ የትምህርት ተቋማት ገበያው እና የማኅበረሰቡ ሥነ ልቦና ሥሪት ተጨማምሮበት እገሌኮ የተማረ ነው ከማስባሉ፣ ግድግዳ ላይ ከሚሰቀል ባለጋውን ፎቶ በላይ የመንግሥት ሠራተኛው የየጊዜውን መስፈርት ለማለፍ ”ተምሮ መገኘት” የሞት የሽረት ጉዳይ ኾነ።
ይህም ዲግሪን በመሸጥ እና በመደለል ለነጋዴዎች እና ደላሎች ተዝቆ የማያልቅ ገቢ ኾነ። ተቋማት እና ኀላፊዎችም ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃን ሊከላከሉ ቀርቶ ራሳቸውም የሚታሙበት ኾነ።አኹን ላይ የአማራ ክልል መንግሥት ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃን በማጣራት ላይ ነው።
የባሕር ዳር ነዋሪው አቶ ይልማ ገበየሁ [ስማቸው የተቀየረ] በቢዝነስ አድምንስትሬሽን ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው፡፡ በልማት ድርጅትም ተቀጥረው ይሠራሉ፡፡ አሚኮ ስለ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ እና ተዛማጅ ጉዳዮች አስተያየታቸውን ጠይቋል፡፡
አቶ ይልማ ሀሰተኛ የትምህርት ”ማስረጃን ሰው ያልለፋበትን የሚያገኝበት ሀሰተኛ የእውቀት ማረጋገጫ” በማለት ገልጸውታል፡፡ ”ተቋማትም ሀገርም በሀሰት የሚመሩበት መሣሪያ” ኾኗልም ብለዋል። ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃን ለማጣራት ሲሠራበት የነበረ ቢኾም ውጤት እንዳልታየበት ነው የገለጹት።
በእውነተኛ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ አልፎ ዲግሪውን የያዘ ሰው ማጣራቱ ሲጀመር ደስ ቢለውም ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ያላቸው ደግሞ እንቅስቃሴውን ለማፈን ሲጥሩ እንደሚስተዋሉ ተናግረዋል፡፡ ይኹን እንጂ በጊዜ ብዛትም ቢኾን ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ሀገር እና ሕዝብን ብቻ ሳይኾን ራሱን ግለሰቡንም እንደሚጎዳ ነው የተናገሩት፡፡
ሰው ሳይለፋ የፈለገውን ዲግሪ የሚያገኝ ከኾነ በጥረታቸው እውቀት የያዙ እና ለሀገር የሚጠቅሙ ሰዎች ይገፋሉ፤ ከገበያው ውጪ ይኾናሉ። ትምህርት ዋጋ ወደ ሚሰጥበት ሀገር ይሰደዳሉም ነው ያሉት፡፡ሲማር ያልታየ ያልተሰማ ሰው በሥራ ቦታ ላይ የተሻለ ደረጃ ደርሶ ሲታይ የሥራ ተነሳሽነትን ይገድላል፤ በእውቀቱ እና በክህሎቱ መሥራት የሚችለውም ወደ ኋላ ይኾናል፤ ሥራም ይበደላል፡፡
ተቋምን ከመምራትም አኳያም ውጤቱን ዝቅተኛ ያደርገዋል፡፡ ለሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ መስፋፋትም መጥፎ አርዓያ ይኾናል፡፡ የትምህርት ማስረጃን በግዢ የያዘ ሰው ባልለፋበት የመኖር ራስ ወዳድነት ያለው በመኾኑ የተቋማዊ እና ሀገራዊ የደኅንነት ምሥጢሮችንም ለራሱ ጥቅም ከመሸጥ ወደ ኋላ አይልም ነው ያሉት፡፡
ባለሀሰተኛ መረጃ መሪዎች እና ሠራተኞች ማኅበረሰቡ በተቋማት እና በሥርዓተ መንግሥት ላይ አመኔታ እንዲያጣ እንደሚያደርጉት ነው የገለጹት፡፡ መንግሥት ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃን ተከታትሎ በማምከን ሀገርን ከጥፋት የሚታደግ፣ ከዘመቻ የወጣ፣ ወጥ አሠራር ማበጀት እንዳለበት ነው አቶ ይልማ ያሳሰቡት፡፡
የትምህርት ተቋማት ሥነ ምግባር ያላቸው ሠራተኞች በመፍጠር እና አሠራርን በመተግበር፣ የመንግሥት ሠራተኞችም ለሥራቸው መንግሥት ላይ ግፊት በማድረግ እና መረጃ በመስጠት ኀላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ነው የገለጹት።
ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ሥር ስለሰደደ ሥርዓት መኾን ጀምሯል ያሉት አቶ ይልማ ኅብረተሰቡ ‘ባጋልጥ ችግር ይደርስብኛል’ ወይም ‘ላይፈታ ነገር….’ በሚል ተስፋ ከመቁረጥ በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የሚደርስበት ጉዳት የበለጠ መኾኑን በመገንዘብ ችግሩን ማውገዝ እና መታገል እንዳለበት ነው የመከሩት፡፡
አቶ ይልማ ለጠቋሚዎች ደኅንነት የሚሰጥ ሥርዓት ሊዘረጋ እንደሚገባም ገልጸዋል። በትምህርት ቤቶችም በራስ ጥረት፣ እውቀት እና አበርክቶ ብቻ መጠቀምን በማስተማር ትውልዱ ሊኮተኮት እንደሚገባ ጭምር ነው ያነሱት።
በአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ኮሚሽን የሰው ሀብት ሕግ መሻሻል እና አቅም ግንባታ ዳይሬክተር አያልነህ አስፋው ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃን የማጥራት ሥራ በክልሉ የሚደረገው የአገልግሎት አሰጣጥ እና የመልካም አሥተዳደር ሪፎርሞች መካከል አንዱ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ግቡም ተገቢ የመንግሥት ሠራተኛ እና መሪን መድቦ የማኅበረሰቡን ፍላጎት የሚያረካ አገልግሎት በመስጠት መልካም አሥተዳደርን ማስፈን መኾኑን ገልጸዋል፡፡
በሂደቱ በርካታ ሥራዎች ይከናወናሉ ያሉት አቶ አያልነህ ፈጻሚ ኮሚቴዎችን እና ተቋማትን መሰየም፣ ግንዛቤ መፍጠር፣ የማጥራቱን ሥራ መሥራት እና ማኅበረሰቡ የሚያነሳውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር በመቅረፍ ርካታን ማሳደግን ጠቅሰዋል።
እንደ አቶ አያልነህ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃን ማጥራት በሦስት ዙር ይጠናቀቃል። ከክልል እስከ ቀበሌ ያለው የመንግሥት ተሿሚ እና የሰው ሀብት አሥተዳደር ቡድን ላይ ያሉ ባለሙያዎች መረጃን ማጥራት እስከ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ይጠናቀቃል።
በሁለተኛው ዙር የክልል እና የዞን የመንግሥት ሠራተኞችን መረጃ፣ በሦስተኛው ዙር ደግሞ የወረዳ እና ቀበሌ የመንግሥት ሠራተኞችን መረጃ ማጣራቱ እንደሚሠራ ገልጸዋል። ከስምንት ዓመት በፊት ተጀምሮ የነበረው መሰል ሥራ የደረሰበት አለመታወቁ እና ውጤታማ አይደለም። የአኹኑስ? ከአኹን በፊት ተጀምሮ የነበረው ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃን የማጣራት ሥራ ከነውስንነቶቹም ቢኾን በርካታ ማስተካከያዎችን ለማድረግ አስችሏል ነው ያሉት፡፡
በሥራው ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን በትምህርትነት እንደሚወሰድም ገልጸዋል፡፡የቀድሞው የትምህርት ማስረጃ ማጣራት በሰዎች ጥቆማ ላይ ተመሥርቶ ነበር ያሉት አቶ አያልነህ የአኹኑ ግን የሁሉም መሪዎች እና የመንግሥት ሠራተኛ የትምህርት ማስረጃ የሚመረመርበት መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ከዩኒቨርሲቲዎች እና የከፍተኛ ትምህርት ማረጋገጫ ኤጀንሲ ጋር በመተባበርም በዲጂታላይዝድ መንገድ ማስረጃዎችን ለማጣራት እንደሚሠራ አንስተዋል፡፡ ችግሮች ቢያጋጥሙም እየታየ እንደሚስተካከል ገልጸዋል፡፡ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃን በማጣራቱ ሁሉም ድርሻ እንዳለው የገለጹት አቶ አያልነህ መንግሥት የጀመረውን ዳር ማድረስ እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል፡፡
የመንግሥት ሠራተኞች አቅርቡ የሚባሉትን ማስረጃ ማቅረብ፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም ደግሞ ትክክለኛ መረጃ በመስጠት መተባበር እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡
በዋሴ ባየ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን