“ለሀገር የሰሩ እና መልካም ዓላማ የነበራቸው መሪዎች ሲያልፉ ራዕያቸው ፍሬ እንዲያፈራ ማድረግ ያስፈልጋል” ሚኒስትር መላኩ አለበል

17

ባሕር ዳር: ሰኔ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ለሀገር ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የሰሩ እና መልካም ዓላማ የነበራቸው አመራሮች ሲያልፉ ሃሳባቸው ሕያው እንዲኾን እና ራዕያቸው መሬት ወርዶ ፍሬ እንዲያፈራ ማስታወስ ይገባል ሲሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ተናገሩ።

በሕዝብ የተጣለባቸውን ኀላፊነት በመወጣት ላይ እንዳሉ በግፍ የተሰውትን የአማራ ክልል የቀድሞ ርዕሰ መስተዳድር አምባቸው መኮንን (ዶ.ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች 6ኛ ዓመት የሰማዕትነት መታሰቢያ መርሐ ግብር “ያለፈውን ማክበር፤ የወደፊቱን መከተል” በሚል መሪ ሐሳብ ተከናውኗል።

በመርሐ ግብሩ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የፌደራል ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኀላፊ ጃንጥራር ዓባይ እና ሌሎች የፌዴራል እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል “ለሀገር ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የሠሩ እና መልካም ዓላማ የነበራቸው መሪዎች ሲያልፉ ራዕያቸው መሬት ወርዶ ፍሬ እንዲያፈራ ማስታወስ ያስፈልጋል” ብለዋል።በየዓመቱ የሰማዕታቱ መታሰቢያ ሲደረግም እነዚህ ዓላማዎቻቸውን ታሳቢ ያደረገ መኾኑን ተናግረዋል።

በዶክተር አምባቸው ስም የተቋቋመው ፋውንዴሽን ሕልማቸው በነበሩት ጤና፣ ትምህርት፣ የሀገር ልማት እና ሰላም ዙርያ ትኩረት አድርጎ እየሠራ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።ትምህርት የሀገርን እድገት፣ ፍትሐዊነት እና የኢትዮጵያን መፃዒ እጣ ፈንታ የሚያረጋግጥ በመኾኑ ሕልማቸውን እውን ለማድረግ የሁሉም ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል።

የዶክተር አምባቸው መኮንን ፋውንዴሽን ሥራ አስኪያጅ መዓዛ አምባቸው በበኩላቸው ፋውንዴሽኑ በጥናት እና ምርምር የታገዘ ሥራ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል።ዶክተር አምባቸው ለሀገር እና ለሕዝብ የሚጠቅም የጠራ ራዕይ እንደነበራቸው በተለያዩ ተቋማት ያከናወኗቸው ተግባራት ሕያው ምስክር መኾናቸውንም አንስተዋል።

በስማቸው ፋውንዴሽን በማቋቋም በሕይወት ቢኖሩ ሊፈጽሟቸው ይችሉ የነበሩትን ሕልሞች ለመተግበር እንቅስቃሴ እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል።ችግኝ በመትከል እንዲታሰቡ የተደረገውም ፋውንዴሽኑ ካሉት የትኩረት መስኮች ዋነኛው አረንጓዴ ልማትን በመደገፍ አሻራችንን ለማሳረፍ ነው ብለዋል።

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ደረጄ እንግዳ በበኩላቸው ዶክተር አምባቸው መኮንን በሕይዎት በነበሩበት ወቅት የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ በመኾን በርካታ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ጠቅሰዋል። በዚህም የእርሳቸው መታሰቢያ እንዲኾን በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ጊቢ ሀገር በቀል እና የፍራፍሬ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር መከናወኑን ገልፀዋል።

የዶክተር አምባቸው መኮንን እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች 6ኛ ዓመት የሰማዕትነት መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ተከናውኗል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአዴት ሕዝብ ለሰላሙ እና ልማቱ እያደረገ ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ።
Next articleሀሰተኛ-ፍካት!